ከፊል ዘመናዊ አናቢነት


ንብ እርባታ ሊባክን የሚችል የተፈጥሮ ሃብትን ወደ ኢኮኖሚ መቀየር የሚያስችል ጥበብና ሳይንስን ማቀናጀት የሚጠይቅ ትልቅ የግብርና ዘርፍ ነው፡፡ በዚህም ማንኛውም ፍጡር ሊያመረርተው ወይም ሊሰራው የማይችላቸውን ነገር ግን በእፅዋት ላይ ያሉ ብናኝና ፈሳሽ ሃብቶችን ወደ ውድና በቀላሉ የማይበላሹ ምርቶች (ማለትም ማር፣ ሰም፣ የንብ ዳቦ፣ የንብ ወተት፣ የንብ ሙጫ፣ የንብ መርዝ) መቀየር ያስችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በብዙዎች ዘንድ አነስተኛ ግምት የሚሰጠው ነገር ግን ከቀጥታ የንብ ውጤት (ምርት) በላይ የሚሰጡት እፅዋትን የማዳቀል ወይም የተራክቦ አገልግሎት ይጠቀሳሉ፡፡ የንብ እርባታ እድሜና ፆታ ሳይለይ በአነስተኛ መነሻ ካፒታል መሰራትና በአጭር ጊዜ ምርት የተሻለ ገቢ ማግኘት ያስችላል፡፡ በተጨማሪም ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የስራ ዘርፍ መሆኑ አንጻራዊ ጠቀሜታውን ከፍ ያደርገዋል፡፡   

ኢትዮጵያ በንብ ቁጥር፣ በማርና ሰም ምርት ከአፍሪካ ቀዳሚ ከሚባሉ ሃገራት ትመደባለች፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ከዘርፉ ምንም የሚጠበቅባትን ያክል እንዳልሰራችና ዘርፉ ለአናቢውም ሆነ ለሃገር ኢኮኖሚ ከ10 በመቶ ያልበለጠ ጥቅም እንዳልሰጠ በዚህም የተነሳ ዘርፉ ያልተነካና ለማዘመንም ሆነ ምርቱን ለማሳደግ ብዙ ሃብት እንደሚገኝ ይታመናል፡፡ ከሃብቶቹ ውስጥ ከ7000 በላይ የሚሆ ለንብ ቀሰምነት የሚውሉ ዕፅዋት ዓይነቶች፣ ከ10 ሚሊዮን የሚልቅ የንብ ቁጥር፣ መሻሻል የሚችል ባህላዊ የአረባብ ዘዴ፣ ልምድ ያላቸው አናቢዎች፣ ከፍተኛ የምርት ፍላጎትና አማራጭ የገበያ መዳረሻዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡  

በንብ እርባታ ውስጥ በአብዛኛው አዕምሮ ላይ የሚመጣውና የሚታወቁት የንብ እርባታ ዘዴዎች በባህላዊ መንገድ በጓሮ ንብ ማርባት፣ በሽግግር ቀፎ እና በዘመናዊ ቀፎ በጓሮ ወይም በተፋሰስ ላይ ንብ ማነብ ናቸው፡፡ በጓሮ በሚያረቡበት ጊዜም ለንብ ጠላቶች መከላከያ፣ ከዝናብና ፀሃይ መከለያ የሚሆን ቤት ወይም የንብ ጋጣ ማዘጋጀት የተለመደ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩት ባሻገር በብዛት ትላልቅ ዛፎች በሚገኙበት ውስን ቦታዎች በዛፍ ላይ ከ2 እስከ 12 የሚደርሱ የባህላዊ ቀፎዎችን ማንጠልጠል የተለመደ ነው፡፡  

ነገር ግን በአማራ ክልል፣ በአዊ ዞን፣ ጓንጓ ወረዳ፣ ከቻግኒ ከተማ ትንሽ ወጣ ብሎ በተለምዶ ራንች ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ ልምድ ያለው አናቢ ተሰርቶ ያየነው የንብ አረባብ ዘዴ ግን የተለየ ነው፡፡  

በምስሉ ላይ እንደምትመለከቱት በአንድ ዛፍ ላይ ለብዙ ህብረ-ንቦች ማስቀመጫ እንዲሁም ከዝናብና ፀሃይ መከለያ የሚሆን በእንጨት በማዘጋጀት አስደማሚ የአንድ ዛፍ የንብ እርባታ ጣቢያ አዘጋጅቷል፡፡ የሚወርደውና የሚወጣው በመሰላል ሲሆን ምንም ዓይነት የንብ ጠላቶች በአካባቢው እንዳይተናኮሉት የዛፉን ግርጌ የተለያዩ የንብ ጠላት መከላከያ ነገሮች (ማለትም አመድ፣ ሽቦ፣ እሾህ የመሳሰሉትን) ያጥረዋል፡፡

በጣም የሚገርመው ነገር በአካባቢው በዛፍ ላይ ቀፎ የመስቀል፣ ማር የመቁረጥና ንቡን የመልቀቅ፤ በድጋሚ ሌላ ቀፎ የመስቀልና ንብ የማጥመድ እንጂ በተደጋጋሚ አንድን ቀፎ ለረዥም ጊዜ መከታተል ልምድ በሌለበት አካባቢ ይህን የአንድ ዛፍ ጣቢያ በማዘጋጀቱ ከፍተኛ የሆነ ምርት በተደጋጋሚ ማምረት ከመቻሉም በላይ ንቦች ቀፏቸውን ለቀው እንደማይሄዱበት ነግሮናል፡፡ ይልቁንም ከሌላ ቀፎ የተሰደዱ ንቦች እየመጡ በወደ አዲስ ቀፎ እንደሚገቡ ከባለቤቱ ለመረዳት ችለናል፡፡  

ስለሆነም በአካባቢው የተንሰራፋውን ንቦችን አጥምዶ የመያዝ አምርቶ የማጥፋት ልምድ የቀለበሰ አሰራር ስለሆነና ከአካባቢው የአረባብ ዘዴ ጋር የተስማማ በመሆኑ በሌሎች አናቢዎችም ቢሰፋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ የመጣውን የንብ ቁጥር፣ የምርት ማሽቆልቆል መታደግ ይቻላልና የታየውን ልምድ ማስፋትና ለሞዴል አናቢዎችም ማበረታታት ይገባል፡፡

አዲሱ ቢሆነኝ

የንብ ተመራማሪ

አንዳሳ እንስሳት ምርምር ማዕከል

addbesh@gmail.com

+251911062859

ምስል 1፡- ተለምዷዊ የንብ አሰቃቀል
ምስል 2 ፡- አዲስ የአንድ ዛፍ ጣቢያ
ምስል 3፡- አዲስ የአንድ ዛፍ ጣቢያ

Published by Addisu Bihonegn

I'm a beekeeping Researcher in Andassa Livestock Research Center, Amhara , Ethiopia. BSc in Animal Sciences at Haramaya University MSc. in Apiculture at Bahirdar University.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: