የንብ ማነብ ጠቀሜታዎች (ክፍል ሁለት)


እንዴት ከረማችሁ ውድ የንብ እርባታ ቡድን ተከታታዮች

ባለፈው ሳምንት የዚህ ቡድን ወደፊት በተከታታይ የንብ እርባታ ትምህርቶችን የምናቀርብ መሆኑን እና ለመግቢያ ያክል ንብ ማነብ ለምን ይጠቅማል? የሚለውን በ3 ዘርፎች ማለትም ጥቅል፣ ልዩ ልዩና አንፃራ በሚል ልናየው እንደምንችል በማመላከት ነበር የተሰነባበትነው፡፡

እነሆ ዛሬ ደግሞ የንብ ማነብ ጠቀሜታዎችን በዘርፍ በዘርፋቸው በሚገባ እናያለን ማለት ነው፡፡

 1. ጥቅል የንብ እርባታ ጥቅሞች

በአጭሩ አስርቱ የንብ እርባታ ጠቀሜታዎች ብለን ልናያቸው እንችላለን፡፡ ለነገሩ ከዚህም በላይ ጥቅሞችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ ነገር ግን ጠቅለል ጠቅለል ተደርገው በአስሩ ዋና ዋና ጠቀሜታዎች ስር ልናካታቸው እንችላለን፡፡ እነሱም፡-

ሀ. እፅዋትን የማዳቀል አገልግሎት

ይህ የንቦች የተፈጥሮን ሚዛን ጠብቀው ለማኖር የሚጠቀሙበት ዋነኛው በጋራ የመጠቃቀም ተፈጥሯዊ ባህርያቸው የተነሳ ሲሆን የሰው ልጅ ከሚጠቀምባቸው የምግብ ዝርዝር ውስጥ 2/3ኛው በንቦች የማዳቀል ተግባር አማካኝነት ፍሬ እንዲሰጥ፣ ፍሬውም ጥራትና ብዛት እንዲኖረው በማድረግ ለሰው ልጅና ለምድራችን ህልውና ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ባደጉት ሃገራት የንቦችን የማዳቀል ተግባር በኢኮኖሚያዊ ትንታኔ ሲሰራላቸው ከማርና ሰም ይልቅ ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያወጡ ወይም የማይተካ የምግብ ዋስትና ሚና እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡ እውቁ የአለማችን ባለምጡቅ አዕምሮው አልበርት አንስታይንም በዚህ ጉዳይ “ምናልባት እንደንብ ያሉ ዋነኛ የእፅዋት አዳቃዮች ከምድር ላይ ቢጠፉ የሰው ልጅ ህልውና ከ4 ዓመት አያልፍም” ብሎ ነበር፡፡

(ይህን የማዳቀል አገልግሎት (Pollination Service) የሚለውን ርዕስ በሰፊው የምንተነትንበት የራሱ ፕሮግራም ይኖረናል፡፡ ያኔ በሚገባ እንበትነዋለን፡፡)

ለ. የተለያዩ የቀፎ ውጤቶች ያስገኛል

ንብን በምናረባበት ጊዜ ተፈጥሯዊ የሆኑ የተለያዩ የንብ/የቀፎ ውጤቶች እናገኛለን፡፡ እነሱም ማር፣ ሰም፣ የንብ ወተት፣ ዞፍ (የንብ ሙጫ)፣ ድኝ/ፅጌ ብናኝ (ርክበ ብናኝ)፣ የንብ መርዝ ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ ለጋ ዕጭና ክፋይ ንብንም እንደ ቀፎ ውጤት ልናያቸው እንችላለን፡፡ በማደግ ላይ ባሉ በተለይም እንደኢትዮጵያ ባሉ ሃገራት ከማር ግፋ ቢልም ከሰም ቀጥታና የሽያጭ ጥቅም ያለፈ ብዙም አልተገፋበትም፡፡ ምናልባትም ይህ በራሱ በዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉም ሆነ የምርት ማስፋፋት ማድረግ ለሚሹ እንደመልካም አጋጣሚ ሊወሰድ ይችላል፡፡ 

ይህንን ርዕስም በተመለከተ ራሱን የቻለ ሰፋ ያለ ፕሮግራም የተያዘለት ነው፡፡ የንብ ውጤቶች፣ ጠቀሜታቸው፣ አመራረታቸው፣ አያያዝና ግብይትን በተመለከተ በሚገባ እንቃኘዋለን፡፡

ሐ. አካባቢን ይጠብቃል /ከአየር መዛባትም መከላከያ ይሆናል

ንቦች በማንኛውም የተፈጥ ሃብት ላይ ምንም አይነት ሽሚያ ስለማያደርጉ ይልቁን የተፈጥሮ ሃብቱ እንዲጠበቅ አስተዋፅኦ ስለሚያደርጉ የአየር መዛባትን ለመከላከል፣ ያልተስተካከለ የዝናብ ስርጭትን ተከትሎ የምርት መቀነስ እንዳይኖር ያግዛሉ፡፡ የዝናብ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ንቦች የሚገኙ ከሆነ ዕፅዋት እድገታቸውን ገትተው በፍጥነት ወደ ምርት ሲገቡ በማዳቀሉ አገልግሎት ደግሞ ንቦች ያግዛሉ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ንቦች አካባቢን ለመጠበቅም ሆነ የአየር ንብረት መዛባትን ለመከላከል ከፍተኛ ጥቅም አላቸው ማለት ነው፡፡  

መ. በአነስተኛ ወጭ መሰራት መቻሉ

የንብ እርባታ ለመነሻ እና መንቀሳቀሻ ካፒታል የሚያስፈልገው ገንዘብ አነስተኛ ስለሆነ ማንኛውም ሰው ለንብ ንድፋት አለርጂክ እስካልሆነ ድረስ ወደ ስራው መግባት ይችላል፡፡ መሰራዊ የሚባሉት ወጪዎችም ለቀፎ፣ ለንብ መንጋ፣ ለመስሪያ ቁሳቁስ ናቸው፡፡ በስራ አጋጣሚ በሚፈጠር አደጋ ወይም የንብ መንጋ ስደት ምክንያት የሚደርሰው አደጋ እና በአናቢው ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖም እንደሌሎቹ የግብርና ዘርፎች ከባድ አይደለም፡፡ በተለይ የትሮፒክ አካባቢ ንቦች ፈጣን የመራባት ባህርይ ስላላቸውና በአጭር ጊዜ ስለሚተኩ ጉዳቱን መቀነስ ይቻላል የሚሉ ጥናቶችም አሉ፡፡  

ሠ. ከቀፎ የምናገኛቸው የተለያዩ ውጤቶች ለገቢ ማስገኛ መዋላቸው

በብዙዎች ዘንድ ዋነኛው የንብ እርባታ ጠቀሜታ ከንብ ውጤቶች ግብይት ገቢ ማግኘት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ የንብ ውጤቶች በአግባቡ ከተዘጋጁና ከተቀመጡ ለረዥም ዓመታት መቆየት ስለሚችሉ የገበያ መዋዠቅን መቋቋም ችለው ለአናቢው የተሻለ ገቢ ያስገኛሉ፡፡ የመሸጥና ያለመሸጥ ወይም በገበያው ላይም የበለጠ የመደራደር አቅም ያጎናፅፋቸዋል፡፡ ይህም ማለት በፈለጉት ጊዜ በአማራጭ ዋጋ አማራጭ ገበያን ማግኘት ያስችላቸዋል ማለት ነው፡፡

ረ. በቀጣይነቱ አስተማማኝ መሆኑ

የንብ እርባታ ከአከባቢ ጋር መዛመዱና ይልቁንም ለአካባቢ ጥበቃ ምቹ በመሆኑ በቀጣይ ሌሎች የግብርና ሥራዎች ጋር በመቀናጀት ለመስራትና የተፈጥሮ ሃብት እንዲያገግም፣ እንዲመለስ ለማድረግ ስለሚያግዝ ቀጣይና አስተማማኝ ነው፡፡

ሰ. ለተለያዩ ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል

የንብ እርባታ ዘርፉ የሚፈጥረውን የሥራ እድል ስንመለከት ሰፋ አድርገን ከአናቢው ባሻገር ልንገነዘብ ይገባል፡፡ ለምሳሌ የንብ እርባታ ዘርፍ ባይኖር የማርና ሰም ነጋዴዎች፣ አቀናባሪዎች እና ቸርቻሪዎች፣ የቀፎና የማናቢያ ቁሳቁስ አምራቾች፣ ጠጅ ቤቶች፣ የሰም አምራቾች፣ ጧፍና ሻማ አዘጋጆች፣ ከንብ ውጤቶች የሚዘጋጁ ሳሙና፣ ሎሺን፣ ቅባት፣ ሻምፖ፣ መድሃኒቶች፣ ህክምና እና የምግብ አቅርቦቶች ከመሳሰሉት ዘርፍ ከተሰማሩት ጀምሮ በመንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተቀጥው የሚሰሩ እንዲሁም በግል በንብ እርባታው ዘርፍ አጋዥ ሆነው የሚሰሩ ሰዎችን ማሰብ አይቻልም ነበር፡፡

ሸ. በአጭር ጊዜ ምርት ለመስራት መቻሉ

በትንሽ ወጪ ስራ መጀመርና ማንቀሳቀስ ብቻ ሳይሆን በአጭር ጊዜ ምርት መስጠቱም እንደዋነኛ ጥቅም ይወሰዳል፡፡ በተለይ የመሬት፣ የግንባታ፣ የቋሚ ዕቃዎች ካፒታል ወጪው እንደሌሎቹ የግብርና ዘርፎ ከፍተኛ አይደለም፡፡  

ቀ. በማንኛውም ፆታና ዕድሜ መስራት መቻሉ

ሌሎች የግብርና ሥራዎች ፆታን የሚለዩ (ለምሳሌ ከፍተኛ ጉልበት የሚፈልጉ ሥራዎች ላይ ወንዶች የሚሰማሩበት)፣ ዕድሜን የሚለዩ (አቅም ሲደክም መሰራት የማይቻሉ ለምሳሌ ማረስ) ናቸው፡፡ ነገር ግን በንብ እርባታ ለሥራ የደረሱ ማናቸውም ሰዎች ለንብ ንድፋት ሰውነታቸው የማይቆጣ መሆኑ (አለርጂክ አለመሆናቸው) ከተረጋገጠ በየትኛውም ፆታ ሊሰራ ይችላል ማለት ነው፡፡ እንዲያውም ለሴቶች ለሥራና መሬት አልባ ወጣቶች፣ ከድህነት ለመውጣት ተመራጭ የሥራ ዘርፍ ነው፡፡

 • ልዩ ልዩ የንብ እርባታ ጥቅሞች

ልዩ ልዩ የንብ እርባታ ጥቅሞችን ስናስብ ከላይ ከተዘረዘሩት አዲስ ሃሳብ ለማምጣት ሳይሆን በተለያየ አተያይ ጠቀሜታውን ጎላ አድርገን እንድናስብ ያስችለናል፡፡

ሀ. የቤተሰብ ገቢ ማስገኛ

 • ንብ እርባታ ለሚሊዮን አናቢዎች ተጨማሪ ገቢ በማስገኘት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል
 • ከ90% በላይ የሚሆነው የማር ምርት ወደ ገበያ ይላካል፡፡ በዚህም አናቢዎች ገቢ ያገኛሉ ማለት ነው፡፡  
 • ሰም እና የንብ መንጋም የገቢ ምንጭ በመሆን ያገለግላሉ፡፡   
 • ከንብ እርባታ የሚገኘው ገቢ ለአዝዕርት (ሰብል ዘር) እና አልባሳት መግዣ፣ ግብር፣ ብድርና መዋጮ ለመክፈል ያገለግላል፡፡ ስለዚህ የእለት ፍጆታና ክፍያ የሚውል ገቢን ማግኘት ያስችለናል ማለት ነው፡፡  

ለ. የሃገር ኢኮኖሚ

 • እንደ ኢትዮጵያ ስንመለከት ማርና ሰም ወደ ውጭ ከሚላኩ የእንስሳት ተዋፅኦዎች ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ስለሆነም ንብ እርባታ በወጪ ንግድ እና ምንዛሬ በኩል የሃገርን ኢኮኖሚ ይደግፋል፡፡

ሐ. የማዳቀል ተግባር

 • የንብ እርባታ ለዋና ዋና የምግብ ሰብሎች በንቦች የማዳቀል አገልግሎት ለሃገራዊ የምግብ ምርት ጭማሪና ጥራት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡   
 • የንቦች አዝዕርትና የምግብ ሰብሎች የማዳቀል አገልግሎት ዋጋ ከማርና ሰም ዋጋ በእጅጉ የተሻለ ነው፡፡
 • ንቦች ተክሎችን፣ ሰብሎችን፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ባያዳቅሉ ኖሮ ብዙ ዓይነት የምግብ ዝርዝሮችን ከመመገቢያ ጠረጴዛዎቻችን ልናጣቸው እንደምንችል ብዙ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡  

መ. የሥራ ዕድል ፈጠራ

ከላይ ያለውን ገለፃ ይመልከቱ

ሠ. ለምግብ ደህንነት እና ድህነት ቅነሳ

 • የምግብ ደህንነት መጠበቅ ማለት ሰብል ማምረት ብቻ ሳይሆን የምግብ ሰብሎችንም ለመግዛት የሚያስችል የፋይናንስ አቅም ማጎልበት ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የንብ ውጤቶች ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ በመሆናቸው የቤተሰብን የምግብ ፍጆታ ሊሸፍን የሚያስችል ገቢ ያስገኛል፡፡  

ረ. ማህበራዊ ጠቀሜታ

 • አናቢዎች በአብዛኛው ለተፍጥሮ ሃብት ካላቸው ተቆርቋሪነትና ጠባቂነት የተነሳ አዋቂ  እና በአካባቢው ከፍተኛ ማህበራዊ ጥቅም የሚሰጡ ስለሆኑ ክብር የሚሰጣቸው ሰዎች ናቸው፡፡  
 • በአንዳንድ አካባቢዎች የንብ መንጋ ቁጥር እንደ ሐብት መለኪያ መስፈርት ስለሚታይ ለክብር መገለጫነት ያገለግላል፡፡
 • አናቢዎች በማርና ሰም የሚዘጋጁ መድሃኒቶች ተፈልጎ የማይታጣባቸው የአካባቢያቸው ባህላዊ ሃኪሞች ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡  

ሰ. የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ

 • ንብ ማነብ ለአካባቢና አየር ንብረት ተስማሚ ሥራ ነው፡፡   
 • የንቦቻቸው ህልውና በተፈጥሮ ሃብቱ ጥበቃ ላይ የተመሰረተ መሆኑን በሚገባ ስለሚገነዘቡ አናቢዎች ከማንኛውም ሰው ይልቅ ስለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና እንክብካቤ ያውቃሉ፣ ያስባሉ፣ ይጠነቀቃሉ፣ ይቆረቆራሉ፣ ይተገብራሉ፡፡    
 • የተፈጥሮ ሃብቱን ለመንከባከብ አናቢዎች ገንዘብ ነክ ምክንያት አላቸው፡፡ ይህም ተፈጥሮ ሃብቱ ሲኖር የህልውናቸው መሰረት የሆኑት ንቦቻቸው ይኖራሉና፡፡   
 • ከሁሉም በላይ ግን ንብ እርባታ ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እንደ ማበረታቻ ነው፡፡ ተፈጥሮ ሃብቱ ለንቦች፤ ንቦችም ለተፈጥሮ ሃብቱ ተመጋጋቢ ተፈላላጊ ናቸው፡፡  
 • አንፃራዊ የንብ እርባታ ጥቅሞች

በዚህ ንዑስ ትምህርት ልናይ የሚገባው ከእንስሳት እርባታ፣ ከሰብል ልማት፣ እና ከመሳሰሉ ሥራዎች ጋር ሲነፃፀር በአንፃራዊነት ያለውን ጠቀሜታ የምንመለከትነት ነው፡፡

 1. ንቦች ባይኖሩ ሊባክኑ የሚችሉ ሃብቶችን ለመጠቀም ያስችለናል
 2. (ማር፣ ሰም፣ የንብ ሙጫ፣ የንብ ወተት፣ ድኝ፣ ማዳቀል ወዘተ)
 3. ሰው የማር ወለላን ከዕፅዋት ሰብስቦ ማዘጋጀት አይችልም፣ የሰፋፊ እርሻ ማሳዎችን እፅዋትን ማዳቀልም አይሆንለት  
 4. የሰው ልጅ ምንም የቴክኖሎጂ ምጥቀት ቢኖረውም በተፈጥሯዊ መንገድ የሚመረተውን የንብ ማር፣ ሰም ወዘተ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሊያዘጋጅ አይችልም፡፡
 5. አብዛኛዎቹ የንብ ውጤቶች ቶሎ የማይበላሹ ናቸው፡፡

ትክክለኛውን የምርት ሂደት ጠብቆ ማምረት ከተቻለ፣ የጥራት ደረጃውን ጠብቆ ማስቀመጥ፣ ማጓጓዝና ማከማቸው ከተቻለ ሁሉም የንብ ውጤቶች ለረዥም ጊዜ መቆየት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በታሪክ የተመዘገበው ማር 300 ዓመት የኖረ ማር ምንም ብልሽት ያልታየበት ተብሎ ይሞገሳል፡፡ ቶሎ የማይበላሹ ምርቶችን (ማር፣ ሰም ወዘተ) ወደገበያ ይዞ የሄደ አንድ አናቢ ወተት፣ አትክልት፣ አሳ፣ እና ሌሎችም ቶሎ የሚበላሹ የግብርና ውጤቶች ይዞ ከሄደው ይልቅ የተሻለ ዋጋ የመደራደር አቅም ይኖረዋል፡፡ ምክንያቱም በዋጋ ካልተስማማ በሌላ ጊዜ ሊሸጠው እንደሚችል አምኖ ይመለሳል እንጂ በርካሽ አይሸጠውም ወይም አይጥለውም፡፡    

 • ከፍተኛ የምግብና መድሃኒት ጠቀሜታ አላቸው

እንደማርና ድኝ ያሉ የንብ ውጤቶች ከፍተኛ የሆነ ቫይታሚን፣ ኢነርጂና ፕሮቲን ያላቸው ስለሆኑ በቀጥታም ይሆን ከሌሎች ምግቦች ጋር በመሆን ለምግብነት ይጠቅማሉ፡፡ ተፈጥሯዊ የመድሃኒትና የመዋቢያ ምርቶችም ከንብ ውጤቶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም የዓለም የተፈጥሯዊ የህክምና ትኩረት ከሳቡት በቀዳሚነት ይመደባል፡፡ ለምሳሌ በንቦችና በንብ ውጤቶች ብቻ ህክምና የሚሰጥባቸው ተቋማትን (Specialized Api-therapy Institutions) ባደጉት ሃገራት እናገኛለን፡፡

 • ንቦች በማዳቀል ተግባራቸው የግብርና ምርቶችን (ሰብሎችን) ምርት ለማሳደግ ይጠቅማሉ፡፡

ማንኛውም እንስሳ መመገብ ይፈልጋል፡፡ ለዚህም በተፈጥ ሃብት ላይ ከፍተኛ ውድመት ያደርሳሉ፡፡ ነገር ግን ንቦች ከማንኛውም እንስሳ የበለጠ የግብርና ምርቶችን ምርት ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ፡፡ ባደጉት ሃገራት በተለይም ሰፋፊ የሰብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ማሳ (እርሻ) ያላቸው አበባ በሚያብብበት ወቅት ንቦችን በጊዜያዊነት ተከራይተው በማሳዎቻቸው መሃል በማስቀመጥ ምርት እንዲጨምርላቸው ያደርጋሉ፡፡ እያንዳንዱ ተክል ያራሱ የሆነ በንቦች ላይ ጥገኝነት መጠን ያለያያል፡፡ አንዳንዶች ሙሉ በሙሉ በንብ ላይ ብቻ ጥገኛ የሆኑ ተክሎች አሉ፡፡   

 1. ከማንኛውም የግብርና ሥራ ጋር የሃብት ውድድር አያደርግም

አንድን ቦታ አንድ ሥራ ልንሰራበት ካሰብን መምረጥ ግድ ይለናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሄክታር መሬት ቢኖረን እንበልና እንስሳት ማርባት ብንፈልግ የትኛውን እንስሳ ይችልልናል ብለን እናስባለን፡፡ አገናዝበን እንመርጥና ወደሥራ እንገባለን፡፡ ከዚህ በኋላ ሌላ ሥራ ልስራበት ብንል አንችልም፡፡ ሰብልም ቢሆን ማለት ነው፡፡ ምክያቱም የቦታ፣ የጊዜ፣ የጉልበት፣ የሃብት ሽሚያ ስለሚኖር አንዱን መምረጥ ግድ ስለሚለን ነው፡፡ አንዳንድ ሥራዎች ደግሞ አንዱ ጠፊ ሌላኛው አጥፊ የሆነ ተቃራኒ ባህርያት አላቸው፡፡ ንቦች ግን የትኛውም የግብርና ሥራ ጋር በተመጋጋቢነት አብሮ ማስኬድ ይቻላል፡፡  

ከሰብል አምራቾች ጋር ብዙ ጊዜ የማያግባቡ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሰብል አምራቹ የንቦች ጉዳይ ሳያሣስበው ወይም በግዴላሽነት ለተባይ ማጥፊያ ያልተፈቀዱትን ፀረ-ተባይ ኬሚካሎች ባልተፈቀደ ጊዜ፣ መጠንና ጥንቃቄ ሲረጭ ይታያል፡፡ ነገር ግን ንቦች ለሚያመርተው ምርት ጭማሪ ምን ያክል አስተዋፅኦ እንዳላቸው ቢረዳ የንብ ጉዳት ጠባቂው ራሱ ሊሆን ይችል ነበር፡፡  

 • የንብ ውጤቶች ከፍተኛ ገቢ ስለሚያስገኙ እንደ ቤተሰብ ገቢ ምንጭና የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማግኛነት ያገለግላሉ

(ከላይ የተሰጠውን ማብራሪያ ይመልከቱ)

 • የምግብ ደህንነትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል
 • ያልተስተካከለ የዝናብ ስርጭት በሚኖርበት ጊዜ ዕፅዋት እድገታቸውን ገታ አድርገው ወደ ፍሬ ማፍራት ሲገቡ ንቦች ደግሞ በማዳቀል ያግዟቸውና ቶሎ ፍሬ ይዘው የዝናብ እጥረቱን እንዲያመልጡ ያደርጓቸዋል፡፡ በደረቃማና ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ዝናቡ አነስተኛ ቢሆመ የሰብል ምርት ማግኘት ምርቱ አነስተኛ ቢሆንም ደግሞ ማር ማግኘት የሚቻለው ለዚህ ነው፡፡  
 • ንቦችም ላልተስተካከለ የዝናብ ስርጭት ጉዳት አነስተኛ ተጠቂ ስለሆኑ ከሌሎች እንስሳት ይልቅ ድርቅን መቋቋምና ራሳቸውን ማስተካከል ይችላሉ፡፡ 
 • የገቢ እና የውጭ ንግድ ዕቃ ዓይነት ለማስፋት ይጠቅማል 
 1. የተፈጥሮ ስነምህዳር ሚዛንን አያዛባም
 2. በአነስተኛ መሬት ሊከናወን ይችላል 
 3. ለምርት መሬት ማስፋፋት (intensification) አገልግሎት ይጠቅማል
 4. የመነሻና መንቀሳቀሻ ካፒታል አነስተኛና አደጋውም ዝቅተኛ ነው 
 5. የዕለት ተዕለት ክትትል አያሻውም 
 6. በየዕለቱና በየሰዓቱ ለማብላት፣ ለማጠጣት፣ ለመጠበቅ፣ ለመንከባከብ ተጨማሪ ጉልበት አያስፈልገውም፡፡ በተጨማሪም በትርፍ ጊዜ ወይም በተደረቢ ሥራነት ሊከናወን ይችላል፡፡  
 7. ፆታና ዕድሜን ሳይለይ ሊሰራ ይችላል፡፡

ስለተከታተላችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡

በሚቀጥለው ስንመለስ ንብ እርባታ በኢትዮጵያ ምን ይመስላል፣ ታሪካዊ ሁኔታውን፣ ያለንን አቅም፣ ያሉብን ተግዳሮቶች ወዘተየሚለውን በሚገባ እናያለን፡፡

ላይክ፣ ሼር፣ በማድረግ እንዲሁም ተጠቃሚ መሆን አለባቸው የምትሏቸውን እዲቀላቀሉ በመጠቆም (suggest በማድረግ) የተጠቃሚውን አባል ቁጥር እንድታሳድጉ እንዲሁም ወደፊት ምን መስተካከልና መካተት እንዳለባቸው አስተያየት በመስጠት እንድትተባበሩን ትጠየቃላችሁ፡፡

በሁሉም ርዕሶች ላይ አለምአቀፍ ተሞክሮዎችንም በማንሳት፣ ጥልቅና ተከታታይ ትንታኔ በመስጠት ለረጅም ጊዜያት አብረን እንቀጥላለን፡፡

ወደፊት በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛዎች (ለምሳሌ በፌስቡክ ቀጥታ ስርጭትና በዩቲዩብ) ለመምጣት ሃሳብ አለን፡፡ ለጊዜው ግን የፌስ ቡክ ግሩፑ (የቡድኑ) https://www.facebook.com/groups/514839721862656 አባል በመሆን ወይም በቴሌግራም ቻናል https://t.me/semonegna በትዊተር ገፅ https://twitter.com/AddisuBihonegn ወይም በቀጥታ ከዌብሳይታችን https://addisubihonegn.wordpress.com/ መከታተል ትችላላችሁ፡፡

መልካም ጊዜ!

ቸር ይግጠመን!! በሰላም እንገናኛለን!!

Published by Addisu Bihonegn

I'm a beekeeping Researcher in Andassa Livestock Research Center, Amhara , Ethiopia. BSc in Animal Sciences at Haramaya University MSc. in Apiculture at Bahirdar University.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: