በዓለ መስቀል፤ (መስከረም፣ የመስቀል ወፍ እና የአደይ አበባ)


የመስቀል በዓል ለኢትዮጵያ  

ኢትዮጵያ በዓለም ፊት ይዛ የምትቀርበውና የራሷ ብቻ መገለጫ የሆኑ፣ በልዩ ሁኔታ የምትታወቅበት ተፈጥሯዊ ፀጋዎች ብዙ ናቸው፡፡ ዘመን የተሻገሩ ቅርሶች፣ አስደናቂ ቤተ-መንግስቶች የአባቶቻችን አሻራ የእኛ የኩራታችን ምክንያት የሆኑ ቅርሶች መለያዎቻችን ናቸው፡፡

በጥበብ ዘመን ያስቆጠሩ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት አምባዎች አድርገዋቸዋል፡፡ እነኚህ ቅርሶች መገለጫዎቻችን ብቻ አይደሉም፡፡ የቱሪስት መስህቦች የቱሪዝም ኢንዱስትሪዎቻችን አቅሞች ናቸው፡፡ እሳት ከሚገነፍልበት የምድር ጥግ ደመና እስከሚጋልብበት የተራሮች አናት መገኛ ነን፡፡ ከሚታየውና ከሚዳሰሰው ድንቅ መስህብ ባሻገር የረቂቅ ባህልም ባለቤት ነን፡፡ አንዱም ዘመን አቀማመራችን ነው፡፡ ጊዜ ቀምረን በዓላታቾቻችን እናከብራለን፡፡ የቀን አቆጣጠር ጥበባችን የብዝሃ-ባህል ማሰሪያችን ነው፡፡ ያለዘመን ስሌት ጥበብ የለም፡፡ የቀን አቆጣጠራችን እንደበርካታ መንፈሳዊ መገለጫዎቻችንና ኩነቶቻችን ሁሉ የማንነታችን መገለጫ ትልቅ ጥበብ ነው፡፡ ጊዜን እንዴት አድርገን እንሰፍረዋለን ወይም እንዴት እንለካለን ካልን በሁለት መንገድ እናያለን፡፡ አንደኛው የፀሐይ፣ የጨረቃና ከዋክብት እና ሌላኛው ደግሞ የእፅዋት የአዝዕርትና አትክልት ደግሞ በሌላ በኩል እናገኛለን፡፡ የምድራችን ቀለም ጭምር ዘመን ቆጥሮ ይነግረናል፡፡ እፅዋትን፣ አዝዕርትና አትክልትን አይተን ዘመንን እንለካለን፡፡

አደይ አበባ ከሀምሌ ነሐሴ ጀምሮ በሚጥለው ሐይለኛ ዝናብና ተያያዥ ምቼ የአየር ሁኔታ እንድትወጣ ያደርጋታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ያለች ባለድርብ መስቀል ወይም ባለ ስምንት አበባ አደይ ነች፡፡ ይህም ክረምቱ አለፈ አበቦቹም ወጡ፡፡ በቅዱስ ያሬድ ዜማን የምናየው ይህንኑ ነው፡፡ የዝናብ ኮቴ ሲሰማ ያዘኑ ይደሰታሉ፣ የተራቡት ይጠግባሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ገበሬ ስራውን ይሰራል፡፡ ካልሆነ ግን (ለሞኝ ሰኔ በጋው መስከረም ክረምቱ እንደሚባለው) ውጤቱ እጅ መዘርጋት ይሆናል ማለት ነው፡፡

ስለመስቀል በዓል አከባበር መነሾ፣ በጽሑፍና በቃል የተላለፉ መረጃዎች እንደሚነግሩን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል በተአምራዊነቱና በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ክብር የተሰጠው በመሆኑ፣ አይሁድ በቅንአት ተነሣሥተው ለ300 ዓመታት ያህል በቆሻሻ መጣያ ጥለውት ነበር። ይሁንና በ326 ዓ/ም የቄሳር ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ኪራቆስ በተባለ አንድ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ ጠቋሚነት፣ መስቀሉ የተጣለበትን አካባቢ ተረዳች። ከዚያም በኋላ ደመራ ደምራ በእሳት አቀጣጥላ ዕጣን ባጨሰች ጊዜ፣ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ከወጣ በኋላ ተመልሶ ያረፈበትን ሥፍራ አስቆፍራ መስቀሉን አውጥታዋለች።

ንግሥተ ዕሌኒ በጭሱ ምልክትነት፣ መስቀሉን ለማውጣት ለሰባት ወራት ያህል ማስቆፈሯን ማለትም  መስከረም 17 ቀን አስጀምራ በመጋቢት 10 ቀን እንዳስወጣቸው ይነገራል። ዛሬ በኦርቶዶክስ ምዕመናን ዘንድ ደመራ የሚደመረውም ይህንን ታሪክ ተከትሎ እንደሆነ የሊቃውንቱ ምስክርነት አለ።

በዓለ መስቀል በክርስትና ኃይማኖት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ የተሰቀለበት መስቀል በአይሁድ ከተቀበረበት ሥፍራ መገኘቱን ማስታወሻ በዓል ሲሆን በምዕራብምሥራቅአብያተ ክርስቲያናት ይሄንን መታሰቢያ መስከረም 3 ቀን ሲያከብሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን ታከብራለች።

በቤተ ክርስቲያናችን ሁለቱም ዕለታት ይከበራሉ፤ በደማቅ ሁኔታና በመጀመሪያ ደረጃ የሚከበረው ግን መስከረም 17 ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት መጋቢት 10 ቀን ሁልጊዜም በዐቢይ ጾም ወቅት የሚውል መሆኑና ለመስቀሉ የተሠራው ቤተ መቅደስ የከበረው መስከረም 17 በመሆኑ ነው፡፡

ይህ የአደባባይ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሁነቶችን አጣምሮ የያዘው የመስቀል በዓል የማይዳሰሱ የዓለም ቅርስ በመሆን በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ የባህልና የትምህርት ድርጅት ተመዝግቧል። ደግሞም በክረምት ወቅት ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱሪስት ፍሰት በአዲስ መልክ የምናስተናግድበት ጅማሮ ነው፡፡

አደይ አበባ ከመስቀል በዓል ጋር ደመራው ላይ የሚደረገው ለምንድን ነው?

መስከረም ባበባው ሠርግ በጭብጨባው ይታወቃል” ይላሉ አበው። አንድም መስከረም ርዕሰ ዓውደ ዓመት፣ የዘመን መለወጫ በመሆኑ ወርኃ አደይ ወወርኃ ጽጌ ተብሏል። እናም ወርኃ መስከረም፣ ኃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን አቅፏል። ከነዚህም ውስጥ ከዕንቁጣጣሽ በዓል ቀጥሎ በሠፊው የሚታወቀው በዓለ መስቀል የተባለው ነው።

መስቀል ምንም እንኳ በክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች ዘንድ፣ የራሱ የሆነ ትርጉም ያለው ቢሆንም ከኃይማኖታዊ ክንዋኔው ባሻገር፣ ባህላዊ በሆነ ገፅታ የሚያከብሩት የኅብረተሰብ ክፍሎች ቀላል የሚባሉ አይደሉም።  መስቀል ለጉራጌ፣ ኢሬቻ፣

ዋናው አደይ አበባ በደመራ በዓል ላይ የሚደረግበት ምክንያት

እሰይ እልል በሉ

አልቀረም ተቀብሮ ተገኘ መስቀሉ

በብርሃን መላት ዓለምን በሙሉ እየተባለ እየተዘመረ በዓሉ ይከብራል፡፡  

የጥል ግድግዳ የፈረሰበት፣ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የታረቀበት፣ የድህነታችን ምልክት የሆነው መስቀል በመገኘቱ የተነሳ ቢጫውም አደይ አበባ ተስፋና ብሩህ ነገር ወደፊት እንደሚጠብቀን አመላካች ነው፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን ሃይማኖታዊ ምክንያቱን ባላውቀውም ትርጉሙ ግን ይህ ይመስለኛል፡፡

የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ የሆነው አደይ አበባ ከምን ዓይነት የዕጽዋት ዝርያ ይመደባል?

ምን ያህል ዝርያዎች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ? እንዴት ይለያል? ምን አይነት ጥቅም እንዳለው?

ምን ያክል ዝርያዎች አሉ?

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-እፅዋት መምህር ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው እንደተናገሩት አደይ አበባ የሚባሉት አንድ አይነት ብቻ ዝርያ ያላቸው ሳይሆኑ ሁለትና ሶስት የሚሆኑ በቤተሰብ ተመሳሳይነት ያላቸው ዝርያዎች ናቸው:: በቤተሰብ የሳይንሳዊ መጠሪያቸው ባይደንስ በሚል ይታወቃሉ:: ባይደንስ ፕሪስቲናሪያ፣ ማክሮፕቴራ፣ ፓቺሎማ፣ ፒሎሳ የሚባሉ አሉ፡፡

የዘርፉ አጥኝዎች በአለም የቁጥር ልዩነት ቢታይም እስከ 300 የሚደርሱ የባይደንስ ዝርያዎች እንዳሉ ጠቁመዋል:: በኦሃዮ ዩኒቨርሲቲ የእጽዋት እና ብዝሃ ህይወት መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን ታደሰ እንደጠቆሙትም ሜክሲኮ እና ደቡብ አሜሪካ እንደሚገኝ አፍሪካው ውስጥ ወደ 64 የባራደንስ ዝርያዎች ሲኖሩ ከነዚህ ውስጥ 21 ያህሉ ዝርያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛሉ:: 21 ውስጥ ወደ 12 ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙ ናቸው:: እነዚህ ደግሞ ባይደንስ ማክሮፕቴራ የሚባለው በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው የአደይ አበባ ዝርያዎች አካል ናቸው::

ኢትዮጵያ ያለው አደይ አበባ ከሌሎቹ እንዴት ይለያል?

የአደይ አበባ ባህርያት

ባይደንስ ማክሮካርፖ የተባሉት በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙት የአደይ አበባ ዝርያዎች ከሌሎች መሰሎቻቸው (የባይደንስ ቤተሰቦች) የሚለዩባቸው ባህርያት አሏቸው:: ዕፅዋቶቹ አንዳቸውን ከሌላቸው ከሚለያቸው መገለጫዎቻቸው መካከል የቅጠሎቻቸው ቁጥር መብዛት እና ማነስ አንዱ ነው:: አንዳነዶቹ የባይደንስ ቤተሰብ የአደይ አበባ ዝርያወች ቅጠሎቻቸው ከሁለት እስከ ሶስት ስንጥቅ ሲኖራቸው አንዳንዶቹ ደግሞ አምስትና ስድስት ስንጥቆች አሏቸው::ሌላው ደግሞ የቅጠሎቻቸው አዘረጋግ ነው::

የአበባዎቻቸው እና የፍሬያቸው ሁኔታም ልዩነቶች ከሚገለፁባቸው መስፈርቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው:: ሌላው ከአባባው ጋር የተያያዘው ልዩነት የቀለም ነው:: የአንዳንድ የአደይ አበባዎች ቀለም ፈዘዝ ያለ ቢጫ ሲሆን የሌሎቹ ቀለም ደመቅ ያለ እና የተለየ ነው:: ከፍሬውም አንፃርም በእኛ አገር የሚገኘው የአደይ አበባ ዝርያ ከሌሎች ዝርያዎች አንፃር ፍሬው ትልቅ መሆኑም ሌላዉ የሚለየው ባህሪ ነው::

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ትክክለኛ አደይ አበባ የምንለው በጣም ልዩ ምስጢርም ያለው ይመስለኛል፡፡ ምናልባትም ጥናት የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል፡፡ የአበባውን ብዛት ስንመለከት ድርብ መስቀል ይመስላል ወይም ስምንት የአበባ ቅጠል ያለው ነው፡፡

በዚህም የተነሳ አደይ አበባ በብዙ ቦታዎች ላይ የንግድ ምልክትና ስያሜ (አደይ አበባ ፎምና ፕላስቲክ)፣ ብሔራዊ አርማ (ስታዲየም) እና አገልግሎት (ኢትዮ ቴሌኮም) ይውላል፡፡

አደይ አበባ ለምን በመስከረም ወር ብቻ ይታያል?

አውሮፓውያን ከዘመን መለወጫቸው ሳምንት በፊት በሚከበረው የገና በዓል በወቅቶች መፈራረቅ የሚከሰተውን በረዶ በጉጉት ይጠብቃሉ፡፡ በረዶ ከጎደለ ቅር ይላቸዋል፡፡ በዓሉ ይደበዝዝባቸዋል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያንም ዘመን በሚለውጡበት መስከረም ወር ተፈጥሮ የምትለግሳቸውን አደይ አበባ በናፍቆት ይጠብቃሉ፡፡ ከአዲስ ዓመት ይልቅ ደግሞ አደይ አበባ በብዛት የምትፈነዳው በመስቀል ነው፡፡

የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ 

ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ

ማን ያውቃል………? ይላል የባለቅኔ መንግሥቱ ለማ ግጥም 

መስቀል አበባ ነው ውብ አበባ

አደይ አበባ ነች ውብ አበባ

ከ870 በላይ የወፍ ዝርያዎች ያላት ኢትዮጵያ 18 የትም ዓለም የሌሉ ብርቅዬ አዕዋፋት መገኛ ነች፡፡ ከነዚህ ውስጥ የመስቀል ወፍ (ተራ ወማይ) አንዷ ነች፡፡ ምግቧን እንደልብ ስለምታገኝ ትታያለች፡፡ ላባዋን ትቀይራለች፡፡ በዚህ ጊዜ የወጣው አዲስ ላባ ደምቆ ይታየናል፡፡

የመስቀል ወፍ ለአይን ያበቃት የመስከረም ውበት ነው፡፡ የመስከረም ውበት ምስጢር አበቦች ናቸው፡፡ መስከረም ምድር በአበቦች ቀለም አዲስ ልብስ የምትለብስበት ነው፡፡ አደይም እንደመስቀል ወፍ የመስከረም ጌጥ ናት፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው የአደይ አበባ ዝርያ የዕድገት ጊዜውን ሲጨርስ የሚሞት ሲሆን ፍሬው ብቻ መሬት ውስጥ ተቀብሮ የሚቀር ነው:: የሌሎች ግን ግንዳቸው ወይም ስራቸው ተርፎ የሚቀር ነው::

ዋናው የአበባ ጊዜ በመስከረም ወቅት የሆነበት ምክንያት ግን የአበባ ማውጣት ዑደታቸው መስከረም ስለሆነ እና የዚህ የአደይ አበባ ዝርያ ፍሬ አፍርቶ ደርቆ ተክሉ ከሞተ በኋላ ፍሬው መሬት ተቀብሮ ከስድስት ወር እስከ ሁለት አመት ሊቆይ ስለሚችል ነው:: ይህ ወቅትም የሽልብታ ጊዜ /የዶርማንሲ ፔሬድ/ ይባላል:: በነዚህ ጊዜያት ውስጥ ምቹ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ብቻ ፍሬው እንደገና እንዲበቅል ያደርጋል ማለት ነው:: ይህም ማለት ለዕፅዋት ብቅለት አስፈላጊ የሆኑት እርጥበት፣ አየርና ሙቀት በበቂ ሁኔታ ሲስተካከል ማለት ነው፡፡ ለማበብ ደግሞ ክረምቱ መውጣት አለበት፡፡ ምንም እንኳን ሐምሌና ነሐሴ ቢበቅልም መስከረም ሳይጠባ አያብብም፡፡

እኛ ብንዘራው ይበቅላል ወይ?

እንደሚታወቀው የዝናብም ይሁን የመስኖ ውሃ ካገኙ በርካታ የሣርና የተክል ዓይነቶች ይበቅላሉ፣ ያብባሉ፣ ያፈራሉ፡፡ የአደይ አበባ አስገራሚው ነገር የቱንም ያክል በበጋ ዝናብ ቢያገኝ ወይም በየትኛውም የመስኖ እርሻ ባለበት አካባቢ አይበቅልም፡፡ ሐምሌ ከገባ ጀምሮ ግን በየእርሻውና በየዳገቱ በተለይ ከሰውና እንስሳት ንክኪ ነፃ የሆኑ ቦታዎች ሁሉ መብቀል ይጀምራል፡፡

አደይ አበባ ለምን ያክል አብቦ ይቆያል?

አበባው አንዴ ካበበ በኋላ እንደፈካ ምድርን አስውቦ የሚቆየው ለረጅም ጊዜ አይደለም:: ቢበዛ ለሶስት ወራት ብቻ ጋራና ሸንተረሩን፤ ሜዳና ተራራውን በተስፋ ሰጪው ቢጫማ ቀለም አስውቦ ይቆይና ይጠፋል:: ይህም ሌላው የአደይ አበቦች መለያ ባህሪ ነው::

አደይ አበባ ማንም ሳይዘራው ረዥም የድርቅና የክረምት ወራትን (የብሉይ ኪዳን ወይም የዓመተ ፍዳ ተምሳሌት) አሳልፎ ዓመቱን ጠብቆ እንደገና ይበቅላል (የሀዲስ ኪዳን ወይም የዓመተ ምህረት ተምሳሌት)። ምድርንም ብናይ ተመሳሳይ ነው፡፡ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከክረምት ወደ ፀደይ ሽግግር ታደርጋለች፡፡ ሰውም (በሃይማኖቱ ስናየው) ከብሉይ ዘመን ወደ ሃዲስ ዘመን ከሞት ወደ ህይወት ከጥፋት ወደ ድኅነት የተለወጠበት ምሳሌ ነው፡፡

የአደይ አበባ ሌላ ጥቅም

ወቅቱ አዲስ አመት መጣሁ መጣሁ እያለ የአውዳመቱ ሽታ በመላ ሰውነታችንን የሚናኝበት ጊዜ እንደመሆኑ መጠን ከአደይ አበባ ጋር የተገናኘ መረጃ ለዚያውም ለህክምና ጥቅም እንደሚሰጥ መስማት ከምንም በላይ ደስ ይላል፡፡

ቴክኖሎጂ ባልመጠቀበት ዘመን ለበሽታዎች ሁሉ ፈውስ በአካበቢያቸው ከሚገኙ እፅዋትና ሌሎች ንጥረ-ነገሮች መድሃኒት እየቀመሙ ከባዱን ዘመን አልፈው ዛሬ ላይ ተሻግረዋል፡፡

አደይ አበባ አካባቢን ከማስጌጥ በተጨማሪ በኢትዮጵያ የባሕል ሕክምና ውስጥ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡

የኦሀዮ ዩኒቨርሲ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን አደይ አበባ ጋራና ሸንተረሩን፤ ሜዳና ተራራውን ከማስጌጥ ያለፈ ጥቅም እንዳለው ተናግረዋል:: አበባው በተለይ በአሩሲና በከፋ አካባቢ ጥቅም ላይ ይውላል፤ በነዚህ አካባቢዎች የአደይ አበባ በስፋት ለደም ማቆሚያት እንደሚውል ተናግረዋል::

ፕሮፌሰሩ ከ30 አመት በፊት በኢትዮተያ ባደረጉት ጥናት የአደይ አበባ በተለይ ሴቶች ወልደው ደም እየፈሰሰ አልቆም ካላቸው ጨቅጭቀው ጭማቂውን እንዲጠጡ በሚደረግበት ጊዜ የሚፈሰውን ደም እንደ ሚያስቆምላቸው መስማታቸውን ተናግረዋል:: ከዚህ በተጨማሪ ፀረ ተዋህስ /Anti- infction/ በመሆን እንደሚያገለግለም ጠቁመዋል::

ሌሎች አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱትም የአደይ አበባ ለስኳር በሽታና ለጭንቅላት ካንሰር ህክምና እንደሚውል ፍንጭ ሰጥተዋል::

አደይ አበባ ለቆዳ ሕክምና ጥንታውያኑ ኢትዮጵያውያን፣ `ጠቢባን` እንደነበሩ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡

ዩኮፒያ የተባለ አንድ በኢትዮጵያ የሚገኝ ግብረ ሰናይ ድርጅት ከአደይ አበባ ክሬም አምርቶ ለገበያ ማቅረቡም ታውቋል:: ክሬሙ ወንዶች ፂማቸው ከተላጩ በኋላ ለማለስለሻነት የሚቀቡት ነው:: ሌላው ከዚህ በአበባ ለሴቶች የተሰራው ክሬም ደግሞ ለማዲያት መከካለያ (ማጥፊያነት) የሚውል መሆኑም ታውቋል::

አዘገጃጀትና አጠቃቀሙ

  • አበባውን አድርቆ በመውቀጥ
  • ዱቄቱን ከቅቤ ጋር መለወስ
  • ውህዱን የተጎዳው ቦታ ላይ መቀባት

ከኢትዮጵያ ውጭ የሚገኙ የተለያዩ የአደይ አበባ ዝርያዎች ለተለያዩ አገልግሎቶች እንደሚውሉም መረጃዎች ይጠቁማሉ:: የአበባው ዝርያ ዋና መገኛ እንደሆነች በሚነገርባት ሜክሲኮ ሴቶች ጨቅጭቀው ፊታቸውን በመቀባት ለውበት መጠበቂያነት ይገለገሉበታል:: ከዚህ በተጨማሪም ከአበባው ተጨምቆ የሚገኘውን ፈሳሽ ለልብስ ማቅለሚያነት ይጠቀሙበታል::

አደይ አበባዎች ከፍተኛ የሆነ ማር ለማምረት የሚውል ንጥረ ነገር በውስጣቸው አላቸው:: በዚህም ምክንያት በማር ምንጭነቱ ይታወቃል:: በተለይም ንቦች በእግሮቻቸው ሰብስበው ወደቀፎዎቻቸው የሚወስዱት ፅጌ ብናኝ ወይም ርክበ ብናኝ የምንለው ዱቄት ከፍተኛ የሆነ የፕሮቲን ይዘት ስላለው ለንቦች ግንባታ በተለይም ለእጭ ማሳደጊያነት ይጠቀሙበታል፡፡ በዚህም ወደዋናው የማር ሥራ ከመግባታቸው በፊት ያላቸውን የሰራተኛ ንብ ቁጥር ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ንቦች ይህን ንጥረ ነገር በመቅሰም የሚሰሩት ማር ለምግብነት ለመድሃኒትነት እና ለሌሎችም በርካታ አገልግሎቶች ግብዓት ይውላል፡፡ ስለዚህ በተዘዋዋሪም መንገድ አደይ አበባ አገልግሎት ሰጠ ማለት ነው፡፡

አደይ አበባ ለሰው ልጅ አስተማሪነት ወይም ማኅበራዊ ፋይዳው

እየሰጠ ካለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታና ከመልዕክቱም ጠንካራነት የተነሳ አደይ አበባ ብዙ ተገጥሞለታል፣ ተዘፍኖለታል፣ በብዙ ቦታዎች ላይ የንግድ ምልክትና ስያሜ (አደይ አበባ ፎምና ፕላስቲክ)፣ ብሔራዊ አርማ (ስታዲየም) እና አገልግሎት (ኢትዮ ቴሌኮም) ይውላል፡፡

ለተሻለ ሕይወት ተስፋ እንዳለ በራሱ መንገድ ከሰዎች ጋር የሚገናኝ የሕይወት መታደስን የሚያመለክት አበባ ነው፡፡ ዓመቱን በሙሉ ሕይወት አልባ ሆኖ የቀረው አንድ ተክል ሕይወትን ለማስመለስ ከቻለ እኛም እንደዚያ ማድረግ እንችላለን፡፡

ሞተ መነሳትን እንማር ከእየሱስ ነው ያለው ቴዲ አፍሮ በግጥሙ  አዎ! እኔ ደግሞ ሞቶ መነሳትን ከአደይ አበባ እንማር ለማለት እወዳለሁ፡፡ ያለፈ ታሪካችን የቱንም ያህል ተስፋ አስቆራጭ እና አሳዛኝ ቢሆኑም አሁንም እንደ አደይ አበባ ህይወታችንን ማደስ እንችላለን፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መነሳት በማየት ከፍተኛ የሆነ መዘናጋት ይታያል፡፡ ነገር ግን በሽታው  አሁንም አብሮን አለ፡፡ የመስቀል በዓል ደግሞ ሰዎች በብዛት የሚገናኙበት የአደባባይ በዓል ስለሆነ ከምንጊዜውም በበለጠ ራሳችንን ከኮሮና በመጠበቅ የመስቀል በዓልን እናክብር፡፡ ለመላው ኢትዮጵያውያን መልካም የመስቀል በዓል ይሁንልን!

ዋቢ ፅሁፎች

ዓምደ ተዋህዶ. መስከረም 26, 2015. የመስቀል በዓል ታሪካዊ አመጣጥ. https://amdetewahdo.wordpress.com/2015/09/26/የመስቀል-በዓል-ታሪካዊ-አመጣጥ/

መ/ር ንዋይ ካሳሁን. ኢኦተቤ የሰ/ት/ቤቶች ማ/መምሪያ. መስቀል ብርሃን ለኩሉ ዓለም.  https://eotcssd.org/dogma-ethiopian-orthodox-tewahedo-church/60-miscellaneous/163-the-holly-cross.html

ሔኖክ ስዩም /ተጓዥ ጋዜጠኛ/ 2019. የመስቀል ወፍና ብርቅዬዋ አደይ አበባ ከመስከረም ምን አገናኛቸው? #Travel Ethiopia “New Year Adey & Yemesekel wef” https://www.youtube.com/watch?v=_4TOaywKa14

dw.com 2017. የአደይ አበባ ባህርያት እና ጥቅሞቹ. https://www.dw.com/am/የአደይ-አበባ-ባህርያት-እና-ጥቅሞቹ/a-40495412

Sci-tech ሳይቴክ 2017. አደይ አበባ ለቆዳ ሕክምና. https://www.facebook.com/SciTechEthiopia/posts/1940298386295797/

በኩር ጋዜጣ 2019. አዲሱ አያሌው. አደይ አበባ. https://www.facebook.com/532782760231143/posts/1307275249448553/

ዋለልኝ አየለ. 2019. የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ. https://www.sewasew.com/p/የመስቀል-ወፍና-የአደይ-አበባ-ነገር  

Published by Addisu Bihonegn

I'm a beekeeping Researcher in Andassa Livestock Research Center, Amhara , Ethiopia. BSc in Animal Sciences at Haramaya University MSc. in Apiculture at Bahirdar University.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: