ሰሞኑን ከዚህም ከዚያም የተቃረሙ ሰሞነኛ ትዝብቶቼን ጠቅለል አድርጌ አቀረብኩላችሁ፡፡ በቴሌግራም ቻናለሌ ላይ ያገኙታል፡፡ ሰሞነኛን ይቀላቀሉ፡፡


ሰሞነኛ ወሬዎች ምን ያክል በኑሯችን ላይ፣ በህይወታችን ላይ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ መገመት ቀላል ነው፡፡ ከማስታውሰው የአባይ ጉዳይም በጣም የጦዘ ሰሞነኛ አጀንዳችን ነበር፡፡ በ2003 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ እንደተጣለ ሰሞን አይን ያወጣ ደራሲ፣ ተዋናይ፣ ፀሃፊ፣ ሰዓሊ፣ ሙዚቀኛ ብቻ በሃገሪቱም ሆነ በተለያዩ የዓለም ሃገራት ያሉ ሁሉ ያላቸውን ለአባይ ለፈፉ፡፡ ሌላውም የኔ ቢጤ ተራ ግለሰብ ያለውን ጉልበት፣ ሃሳብ፣ ገንዘብ፣ ሞራል ሁሉ በመረባበር ለገሱ፡፡ አስታውሳለሁ ቦንድ ግዥ ማለት እንኳን ምን ማለት እንደሆነ ያወቅነው በዚያ ሰሞን ነበር፡፡ አባይ… አባይ… አባይ… ሁሉ ሁሉ ነገር አባይ አባይ ሸተተ፡፡ ያደጉት ሃገራት ጭምር በራሳችን አቅም ድህነታችንን ተረት ልናደርግ መወሰናችንን እና በሙሉ ልብ ግድቡን መገንባት መጀመራችንን ሲያዩ እጅ ሰጡ፡፡ እናም የአባይ ጉዳይ ውሎ ሲያድር ሰሞነኛነቱና ከህዝባዊነቱ እያፈገፈገ ወደ መንግስታዊነቱ አደላ፡፡ በተለይ ደግሞ መዋጮዎች የገቡበት ስምጥ ሲጠፋና በታቀደው ጊዜም ያልተከናወነ መስሎ በታየበት ሁናቴ የሰው ሁሉ ተስፋ መሸርሸር ጀመረ፡፡ ሌላም የማይነካካ ጉዳይ ይኖራል፡፡

እንዲህ እንዲህ እያለ ከዓመታት በኋላ ለምክንያቱ የተለያየ መላ ምት የሚሰጠው የጣና ላይ አረም ወይም እምቦጭ ተከሰተና ሰሞነኛ የመገናኛ ብዙሃንና የማህበራዊ ድረ-ገጾች ርዕሰ አንቀጽ ጉዳይ፣ የዘጋቢና የውይይት ፕሮግራሞች ሁሉ ማድመቂያ ሆነ፡፡ በዚህም የጥበበኞች ሚና አባይን ባነገሱበተት ልክ ጣናን እንታደግ ለማለት አልለገሙም፡፡ በአርቲስቶቻችን ጣና ታመመ  ድረሱ አዋጅ ከቤቱ ተኝቶ የቀረ ያለ አይመስልም፡፡ ከተለያዩ ቦታዎች ጣናን በመጎብኘት የእንታደገው ድምጻቸውን ሲለግሱ፣ እንባቸውን ሲያፈሱ መንግስትም የጣና እንባ ጠባቂ የሆነ ተቋም እስከማቋቋም ድረስ ትኩረት ሰጠው፡፡ ህዝባዊ ሆነ ማለት አይደል፡፡ እየቆየ ግን በሌሎች ሰሞነኛ ጉዳች እየተለባበሰና እየደበዘዘ መጣና የጣና ዳር ነዋሪዎች ብቻ ጉዳይ ሆኖ ቀረ፡፡

ያም ሆነ ሌላ ጉዳይ ብዙ ብዙ ጉዳይ አለፈና ሌላ ትኩስ ዓለም ዓቀፍ ሰሞነኛ አጀንዳ ከች አለላችሁ፡፡ ያልታሰበ፣ ያልተጠበቀ፣ የበደላችን የግፋችን፣ የሃጢአታችን በቃችሁ የሚል ማስታገሻና ትምህርት መስጫ የሚሆን ከቁጥጥራችን ውጪ በሆነ ቅንጣጢት አማካኝነት የሚተላለፍ ኮሮና ቫይረስ ወይም ኮቪድ-19 የሚባል ጅምላ ጨራሽ መድሃኒትም ሆነ ክትባት ያልተገኘለት በሺታ ከወደ ቻይና ውሃን ግዛት መነሻውን አድርጎ በለሆሳስ ዓለምን እያዳረሰ መጣ፡፡ መጣና ስንቱን ቱር ያለ ቱሪናፋ ሁሉ ሰኞና ማክሰኞ ሳይቀር ቱታና ነጠላ ጫማ አስለብሶ ከቤቱ አዋለው መሰላችሁ፡፡ ይህ በሽታ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ነው ተብሎ በታወጀ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከድምፅ በፈጠነ ሞገደኛ አካሄድ ዓለምን አዳርሷል፡፡ ቀስ ቀስ እያለ የሚጨምረው የታማሚ ቁጥር ሽፋን ሃገራትን ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ሲገቡ አየር መንገዳቸውን፣ መተላለፊያ በሮቻቸውን ቢዘጉ አልተመለሰም፡፡ ያለው አማራጭ ቤት ዘግቶ ለ14 ቀን ሱባዔ በቤት መከተት ነው ተባለና ይህም ፋሽን እስኪመስል ድረስ የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆኑ ሁሉም ሃገራት ዜጎቻቸውን ሰበሰቡ፡፡ የኛም ሃገር ዘግይታም ቢሆን ለዘብ ያለ አዋጅ ቢጤ አስተላልፋለች፡፡

ይህ ሰሞነኛ ጉዳይ በሳምንት ወይም ቢጠና በወር ብን ብሎ የሚጠፋ፣ ወይም ወደኛ ሃገር የማይገባ ግን በመንግስት አስገዳጅ ትዕዛዝ ብቻ ከቤት ቁጭ እንድንል የታዘዝን ስለመሰለው ቀለል አድርጎ ያየው ይበዛል፡፡ ውሎ ሲያድር ግን ነገር ሁሉ ባልተጠበቀ ሁኔታ የምናየውን እያየን ነው፡፡ የአዲስ ተጠቂ ቁጥር በወር በድምሩ የተመዘገበውን የሚበልጥ ቁጥር በ24 ሰዓት መመዝገብ ጀመረ፡፡ እናም ይህም ያልፋል ተብሎ በተስፋ የሚጠበቅ ቢሆንም አንዳንድ የአዲስ ታማሚ እና ሟች ቁጥሮች ድንገተኛ መጨመር፣ የጉዞ ታሪክና ንክኪ የሌላቸው ታማሚዎች ማሻቀብ፣ የሃኪሞች በበሽታው መያዝና አንዳንዶች እረፍት ወይም መልቀቂያ መጠየቅ፣ ከሥራና ኢኮኖሚዉ መቀዛቀዝ ጋር በተያያዘም የእርዳታን ልገሳ ቀጣይነት መቀነስ እንደአሉታዊ ተወስደዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የህብረተሰቡ ድንጋጤ መቀነስ ደግሞ ከበፊቱ ይልቅ በጥንቃቄ መቀዛቀዝና መዘናጋት እያሳየ መጥቷል፡፡

እና ደግሞ የምን ኮቪድ ያሰኘ፣ ዓለምን ደብዝዞ ባልጠፋው ዘረኝነት የናጠ ክስተት ከወደ ዴሚክራሲ ቁንጮ ነኝ ባይዋ አሜሪካ ሚኒያፖሊስ ግዛት አዲስ አስደንጋጭ ነገር ተከሰተ፡፡ ጆርጅ ፍሮይድ የተባለ ጥቁር በአንድ ነጭ ፖሊስ አስፋልት ላይ ተጥሎ አንገቱ ላይ እንዳይፈናፈን በእግሩ በመጫን ኢሰብአዊ በሆነ መንገድ እባክዎ መተንፈስ አልችልም Please “I can’t breathe” እያለ ለሞት ተላልፎ ተሰጠ፡፡ በዚህች ቅፅበት በተቀረፀ ቪዲዮ አማካኝነት ዓለም ተገለባበጠች፡፡ የሃገረ አሜሪካ ግዛቶች ጎዳናዎች በሙሉ በተቃውሞ ሰልፈኞች ተጥለቀለቁ፡፡ ነጮች ተንበርክከው እስካሁን ለበደልናችሁ ሁሉ ይቅርታ አድርጉለን ቢሉም ሰሚ የለም፡፡ ዘለፋ፣ ዘረፋ፣ ማብጠልጠል፣ ማቃጠል፣ ምን አደከማችሁ ምስቅልቅል ያለ አዲስ ጉዳይ በኮሮና አዲስ ተጠቂና ሟች ቁጥር ዓለምን የምትመራው አሜሪካን ገጠማት፡፡ ወይ አሜሪካ…  ምኑን ትጨብጠው

በዚህ ሰሞን ደግሞ የጣና ጉዳይ እደገና ያገረሸ ይመስላል፡፡ ዶሴውን ከተቀመጠበት አቧራውንም ቢሆን አራግፎ አጀንዳ መፍጠር ያውቅበታል፡፡ ሁሉም ሰው ህዝቡን፣ በተለይም መንግስትን ተጠያዊ በማድረግ ይወቅሳል፡፡ እኔ ግን ትዝብቴም ራሱን ጣናን ነው፡፡ እንዲህ ታዘብኩት…

በ12/02/2010 ዓ.ም የጣና የውሃ ላይ እምቦጭ ወቅታዊ ሁኔታ ቅኝት ጉዞ ባደረግንበት ወቅት የተጻፈ ነው፡፡ በጣና ላይ ምንም ጠተሸለ ለውጥ ስላልመጣ እኔም በፅሁፌ ላይ ምንም ማሻሻያ አላደረግኩም… በጊዜው የተጻፈውን እንዳለ አቀረብኩት፡፡

ክፍል 1 https://www.facebook.com/addisu.bihonegn/posts/1535902299808701

ክፍል 2 https://www.facebook.com/addisu.bihonegn/posts/2558968184168769

ጣናን ግን ታዘብኩት

ታመመ አሉኝ ጣና ይሄው እኔም አየሁ እውነትም ታመሃል

አልሸነፍም ባይ ለውሃ የሚሞት ትውልድን አጥተሃል

ታሪክ ስለ ውሃ ተፅፎ እንዳየነው

ሰው ነው ሟች ለውሃ ህይወቴ ነው ላለው

ለጠብታ ውሃ ላገር ፍቅር ካሳ ጠብታ ደም ሰጥቶ

ህይወት ይታደጋል፣ ትውልድን ያድናል ሌላ ትውልድ አጥቶ

ዛሬ ግን…

በከፋው ሰማይ ስር ህይወት አሸልባ

በዝምታ ልጓም ዓለም ተሸብባ

ሃገር ሁሉ አድሞ ዝም ጭጭ ማለቱ ምን ይሆን ሃሳቡ

ከጣና ጨልፎ ከደሙ ለመንፃት ዳር ላይ መታጠቡ

መነሻን ረስቶ…

ውሃ ስንቅን ትቶ…

ከቶ መድረሻ አልባ ወደ ረዥም ጉዞ

ግንጥል ጌጥ ማንጠልጠል

ድንበር የለሽ ሃገር… ደረቅ ባህር ይዞ

የሁላችንም ሳቅ እዚህ ሃይቅ ላይ ነው

የሁላችን ውበት እዚህ ባህር ላይ ነው

የሁላችን ህይወት እዚህ ውሃ ላይ ነው

በህመምህ ታመን ጥበብ ተገፈፈ… መልካችን ረገፈ

በበደልህ ስሜት እጃችን ታጠፈ… ሞታችን ገዘፈ

ጣናን ግን ታዘብኩት …

ጣናን ግን ታዘብኩት …

በጀንበር ዝቅዝቀት

የምሽትን ድባብ

በስርቅርቅ ፀሃይ ውበት አጎናፅፎ

የፀሃፊን ብዕር እያሽሞነሞነ

የሰዓሊን ሸራ እያሰማመረ

ልብን የሚያሸፍት ቅኔ አቀብሎ አልፎ

ዛሬ እንዴት ዝም ይላል ጠላቱን አግዝፎ?  

ዛሬ እንዴት ዝም አለ ራሱ ሲታመም

በእራፊ ጨርቅ ላይ በደረቀው ቀለም

በነጠፈ ብዕር በስንብት ዓለም

ልብ የሚል ሰው ካለ

“ለሰሚ አሰማልኝ ህመሜን ይታመም

ቅኔየን ዝራልኝ …

ፍቅሬን ዘምርልኝ

ልታድነኝ ባትችል ለስንብት ናልኝ”

ብሎ ማልቀስ የለም?

ጣናን ግን ታዘብኩት …

ጣና ዳር ላይ ቆሜ ነገን አሰብኩና

አለቀስኩኝ ዛሬ

ጣና ዳር ላይ ቆሜ ኢትዮጵያን አስቤ

አለቀስኩኝ ዛሬ

ይሄው…

እኔም ልመለስ ነው

ቃልህን ሳልሰማ ትዝብትና እምባየን

በቁጭት ቋጥሬ

ጠቅለል አድርጌ ለዛሬ የታዘብኩትን ሰሞነኛ ወጌን ጨረስኩ… ቸር እንሰንብት እንጂ ሰሞነኛ ወሬ አይጠፋምና ከሰሞኑ እመለሳለሁ፡፡

ግንቦት 26/2012

ባህርዳር

Published by Addisu Bihonegn

I'm a beekeeping Researcher in Andassa Livestock Research Center, Amhara , Ethiopia. BSc in Animal Sciences at Haramaya University MSc. in Apiculture at Bahirdar University.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: