መንገድ መሪ ህዝብ ስለመንገድ ተነሳ!


ImageImage48109_452284874878942_272409193_nP1130924P1130925P1130927P1130942 P1130934

P1130891 - Copy

መንገድ መሪ ህዝብ ስለመንገድ ተነሳ!ሰቆጣ – 20/11/2005

አሁን የማወጋችሁ በዋግኽምራ ዋና ከተማ በሆነችው በሰቆጣ ከተማ ስለተካሄደው “ሊሰራ ያለ መንገዳችን ባልታወቀ ምክንያት ቀረብን፡፡ ይህስ ለምን!” ብሎ ስለተነሳ ህዝብ ነው፡፡ “ደግሞ ሰቆጣ የት ናት?” የሚል አይጠፋም መቼም፡፡ ለነገሩ “ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር አለች?” የሚሉስ አሉ አይደል? ምን ይደንቃል? ለማንኛውም ወደ ቁምነገሩ ልውሰዳችሁ፡፡ አይ! ቁምነገር አልኩ… ከቁብ ላልተቆጠረ ቁምነገር… ወደ ‘ወጉ’ ብላችሁ ይቀለኛል፡፡

እንደትናንት ማታ አስከተማ (በላሊበላና ሰቆጣ መካከል ያለች የዋግኽምራ አንድ ወረዳ ነች) ለስራ ሄጄ ሲያወሩ ሰማሁ፡፡ ነገ በጠዋት የመንገድ ሥራው በመቅረቱ የተሰማንን ስሜት ለመግለፅ ሰቆጣ ሰልፍ ስላለ ያንን ለመቀላቀል እንሄዳለን፡፡ ከዚህ በፊትም አንድ መኪና ሙሉ ሰው ሄዷል፡፡

ሰቆጣም ስመለስ ይህንኑ ወሬ በተባራሪ ጆሮዬ ጥልቅ አለ፡፡ ወሬው ሲደጋገም እውነት ነው ብዬ  ስላመንኩ ማለዳ ተነስቼ ጆሮዬን ለሰልፈኞች ድምፅ አዘጋጀሁት፡፡

ከማለዳው ገና ወፍ ሳይንጫጫ ተነስተው ሲቀሰቅሱና ሲያስተባብሩ የነበሩት ትንሽ ሰዎች ትንሽ መፈክሮችን ይዘው ሲጀምሩ ሰማሁ፤ መስማት እየፈለግኩ ስለነበር አላዳገምኩም፡፡ ከተኛሁበት ተነስቼ እነሱ ያሉበት ለመድረስ ያንን ኮረኮንች ቁልቁለት እንዴት እንደወርኩት አላውቅም ወይም አላስታውስም – ለምን? ምን እንደፈነቀለኝና እንደገፋኝ እንጃ! ወሬ እንዳያመልጠኝ አልልም መቼም፡፡

እናላችሁ ሰልፉ እንደወራጅ ወንዝ ገባር እንደሚሞላው እየበዛ እየበዛ እየበዛ ከ3 ወደ 30 ወደ 300 ወደ 3000 እያለ ሄደ፡፡ ከዚያ በላይ መገመት አልቻልኩም እንጂ የመጣው ህዝብ ብዛት ከ4000 አያንስም፡፡ ከጋዝጊብላ ወረዳ/አስከተማ የመጣውን ጨምሮ፡፡ እናንተዬ ስንቱ ውስጥ ወስጡን ሆድ ሆዱን እየበላው ኖሯል፡፡

ሰቆጣ ማለት… ለብአዴን

ሰቆጣ ማለት… ለኢህአዴግ

ሰቆጣ ማለት… ለኢትዮጵያ ህዝብ

ህዝቡ በደርግ መንግስት የወያኔ መደበቂያ ሆኗል በሚል ከ11 ጊዜ በላይ በቦምብ ተጨፍጭፎበታል… የሰውና የእንስሳ ደም ባንድ ላይ ተቀላቅሎ ጎርፎበታል፡፡

ስንቅና ትጥቁ ይቅርና ህይወታቸውን ያለስስት ለነፃነት ለሰላምና ዴሞክራሲ ሲሉ … ሃብት ንብረታቸውን ሳይቀር ይዘው ወደ ትግል የተቀላቀሉ ጀግኖች ያፈራች ሃገር!! በትግሉ ያልተሳተፈ የምንስ ጠላት በሉት!!

በእጃቸው ፈጭተው ጋግረው ስንቅ ከማቀበል አልፎ ወፍጮአቸውን ፈታትተው እንደትግሉ ሁኔታ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በትከሻቸው የተሸከሙ የእውነት እውነተኛ ታጋዮች ያፈራች ማህፀን ነች፡፡ ሰቆጣ !

በ1977 ዓ.ም የኢትዮጵያን ስም የቀየረ ያን ያክል ድርቅ ስታስተናግድና ያ ሁሉ ህዝብ ሲያልቅ የተረፈው ህዝብ በረሃብ አንጀቱ ኮረም ድረስ ነበር ሄዶ መጠለያ የሰፈረው… አንድም ደርግ ሰቆጣን ስላልተቆጣጠራት (የጦርነት ቀጠና እና የኢህአዴግ ምሽግ ስለነበረች) አንድም ደግሞ የዕለት ጉርሱን ለማድረስ መንገድ ስላልነበራት፡፡

ከያንዳንዱ ቤተሰብ ቢያንስ ቢያንስ አንድ ሰው በደርግ ጭፍጨፋ አለያም በትግሉ ተሳትፎ የገበረች ሃገር! ሙሉ ቤተሰብ ያለቀበት አለያም የታገለ ቁጥር ስፍር የለውም፡፡

አሁንስ ቢሆን የኢህአዴግን ፖሊሲና ስትራቴጂ በማስፈፀም… እንከን የማይወጣለት ደጋፊ ህዝብ፣ ያሉትን ሳያቅማማ የሚፈፅም የዋህ ህዝብ ነው፡፡

እና ለዚህ ህዝብ አንድ መንገድ… መንገድማ ለትግል ደፋ ቀና ስትል የነበረች ሃገር ማን ዞር ብሎ ይያት… መኪና የሚሄድበት መንገድ ቢታጣ መኪናውን ፈታትተው በጀርባቸው ተሸክመው ወንዝ ያሻገሩ ጀግና የትግል ጓዶችን ያፈራች ሃገር እንዴት ስለመንገድ ትለምናለች?????

የገረመኝ እኮ ማን ነው ማንን የሚለምነው…? ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል የሚሉት መብታችንስ የት ሄዶ ነው?

አሁን እስኪ በሞታችሁ ሰቆጣ የትግል ታሪክ ዶክመንተሪ ፊልም የሚሰራባት እንጂ ልማት የሚሰራባት እንዳትሆን ማን ከለከላት፡፡

እህህህህህ… ቁስል አለብን እባካችሁ… ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው ነው የሚሉት አባቶች… መፃፍ ሁሉ አቃተኝ እኮ እናንተዬ!

ለማንኛውም ብሶቴን ገታ ላድርግና ወደ ትዝብቴ ልውሰዳችሁ…

የህዝቡ ቁጥር ለቁጥርም ለቁጥጥርም ሲያስቸግር ከአደባባያችንን እስከ መታያችን (ፈረስ መጋለቢያ) ሁለት ያክል ጊዜ እንደተዞረ ወደ አለቆቻችን ቢሮ (ወደ መስተዳድር) ሄድን!! ቀድመው የሰሟት ጉዳይ ስለሆነች ሁሉም ባይባልም አብዛኞቹ የምክር ቤት ስብሰባና የወዳጆቻቸው ሰርግ ጊዜ የሚለብሷትን ሱፍና ከረባት ለብሰዋል፡፡ ጋዜጠኞች አሉ ተብለዋል ለካ! ለትዝብት ይሆናል ብዬ ሰረቅ አርጌ ፎቶ አነሳኋቸው፡፡ ህዝቡ ሁሉ ወደነሱ ዞሮ ጥያቄውን በመፈክር ሲያዥጎደጉደው ጭራሽ ተጀነኑ!! በምክር ቤት አዳራሽ በኩል ሂዱ አሉት… ይህ የዋህ ህዝብ እንደጉንዳን ሰልፉን እንኳን ሳያዛባ የተባለው ቦታ ሄደ፡፡ ለካ እንደዚያ ያሉት እነሱ እንደ ገዢነታቸው ከፍ ያለውን ቦታ ይዘው እንደሙሽራ ተንቀባረው ጨፋሪውን ህዝብ ቁልቁል ለማየት ነበር… ወይም ማን መጣ ማን በጣም ፎከረ (መፈክር አሰማ) ለመታዘብ ኖሯል፡፡ ደግሞም ተሳክቷል፡፡ ለኔ እንደገባኝ ነው ግን!

መፈክሮች

  • መለስ ያቀደውን ተተኪው ትውልድ ሊሰራው፣ ሊያስቀጥለው እንጂ ሊያፈርሰው፣ ሊያደናቅፈው አይገባም!
  • የቆሰልን የደማን የታገልን ስለሆነ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ያገኘነውን መንገድ ልንነጠቅ አይገባም!
  • ቃል ከተገባልን መንገዱ ይሰራልን!
  • ከላሊበላ ሰቆጣ ያለው መንገድ አይናችን ነው… አይናችንን ልንነጠቅ፣ ልንቀማ፣ ልንታገድ አይገባም!

ህዝቡ በቡድን በቡድን እየሆነ የሚያሰማውን ድምፅ በአንድ ድምፅ ማጉያ እንዲቀበል ተደረገ… ለካሜራ እንዲመች ሁላችሁም ፊታችሁን ወደኋላ አዙሩ ተባለ… ሁሉም ዞር! (ከዚህ በላይ የዋህነት አለ) ለኔስ ምንም እንኳ መብታችን ቢሆንም የተቀነባበረ ሰልፍ እስኪመስለኝ ድረስ ተጠራጥሬያለሁ… ምክንያቱም ያየሁት ነገር ነው… ዝም ብላችሁ ገምቱ… ይሄ ለመፃፍ አይመችም!! ኋላም ቀረፃውን ወደ ባለስልጣናት ሲያደርጉ ዙሩ ተብለናል፡፡ አሁንስ ማን አለ የማይዞር?…ማንም!

የህዝብ ተወካይ የሆኑት አንድ ባለሃብት – አቶ ሞገስ በሪሁን ይባላሉ – “የዋግ ህዝብ ጥያቄ” አሉና የሚከተለውን በንባብ አሰሙ፡፡ እኔም ያነበቡትን ወረቀት መጨረሻ ላይ ፎቶኮፒ ስላደረግኩት እንደወረደ ፅፌዋለሁ፡፡ ከመፈክሩ ይልቅ ፅሁፉ የተለሳለሰ ጥያቄ ይመስላል፡፡

ከህዝብ የቀረበ ጥያቄ

ህጋዊ እውቅና ባገኘው ሰላማዊ ሰልፍ የወጣውና ያልወጣው የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ ህዝብ ጥያቄ እንደሚከተለው ይሆናል፡፡

ዞናችን የነበረበትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮ በርካቶቹ በመንግስታችን የተመለሱ መሆናቸው ማንም ህሊና ያለው ሰው ሊክደው የማይችል ጉዳይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሃገራችን ኢትዮጵያ ደረጃውን የጠበቀ መንገድ የሌላት ብቸኛዋ ዞን ዋግኽምራ ስትሆን በቅርቡ በ2004 ዓ.ም ልማታዊ መንግስታችን ከጋሸና-ላሊበላ-ሰቆጣ እንዲሰራ በተፈቀደው መሰረት፣ የደዛይን፣ የአፈር ምርመራና የማህበረሰብ ጥናት ኮር በተባለ የመንገድ ጥናት ድርጅት ተጠናቆ ለህዝብ ይፋ ባመድረግ ሥራው ሊጀመር ጫፍ በደረሰበት ሰዓት ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ በመሰረዙ በህዝብ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ አሳድሯል፡፡ በመሆኑም፣

  1. የተሰረዘበት ምክንያት ለህዝብ ንዲገለፅ
  2. ፕሮጀክቱ ከጋሸና-ላሊበላ-ሰቆጣ ሆኖ ሳለ ከጋሸና ላሊበላ ያለውን ብቻ በመለየት ስራው እንዲጀመር የተደረገበት ምክንያት ይገለፅልን
  3. ዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በዓለም በዩኔስኮ በተመዘገቡ ቅርሶች ላሊበላና አክሱም መካከል የሚገኝ በመሆኑ የዚህ መንገድ መሰራት ሃገራዊ ፋይዳ እንዳለው እየታወቀ ምላሽ አለማግኘቱ ምንድን ነው?
  4. መንገድን ከማጠናከር ህዝቡ እንዲጠቀም ከማድረግ ውጭ ለህዝቡ ልማት የሚቀርብ ሌላ ምን አማራጭ አለው?

ጭብጨባው ዳር እስከዳር አስተጋባ፡፡

ከዚያ በኋላ የሆነው ምን ነበር… አዎ! የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ ሃላፊ መልስ ይሰጣሉና ዝም በሉ ተባለ፡፡ ሁ…ሉ…ም… ዝ…………ም!

ጋዜጠኞች ስለማይክ አያያዝ ስለንግግርና ድምፅ መጠን (መናገር ሰላለባቸው ፍሬ ቃል ሁሉ) የግማሽ ደቂቃ ገለፃ ሰጡና በእጅ ምልክት ይቀጥሉ ተባሉ… ምክትል አስተዳዳሪያችንን!! በሃሳቤ ምን ሊሉ እንደሚችሉ እየገመትኩ ነበር… እርሳቸውን ሆኜ አሰብኩ… ጥያቄያችሁን ለበላይ አካል እናቀርባለን ይላሉ ስል የሚከተለውን ብለው እርፍ!!

ያሉትን ቃል በቃል ባይሆንም ሃሳቡን እንዲህ ስከትበው… እህህ! እሽ ያው ጥያቄያችሁ ትክክልና ተገቢ ነው፡፡ ጥያቄያችሁንም በስነስርዓት አቅርባችኋል፡፡ ነገር ግን መንገዱ አይሰራም የተባለበት ምክንያት ያው… እ… በበጀት እጥረት ነው (ህዝቡ ሆሆሆሆሆሆ – አሁንስ ድራማው የገባቸው መሰለኝ) በዚህ መሃል ጋዜጠኛው ቀረፃውን አቋርጦ ወደ ጆሯቸው ጠጋ አለና ማለት ያለባቸውን ነገራቸው፡፡ በጆሯቸው ቢሆንም የሚነግራቸው የያዙትን ማይክ ድምፁን ስላልዘጉት ወይም ዞር ሰላላደረጉት የጋዜጠኛው ምክር ለየዋሁ ህዝብ ጆሮም ደርሷል፡፡ መልሰን በርሳቸው አንደበት ሰማነው፡፡ እሽ አሉ… (እኛን ዝም ለማሰኘት) ጋዜጠኛው ቶሎ ወደ ካሜራው ሄደና የጅ ምልክት ሰጣቸው፡፡ እሽ ያው ጥያቄያችሁን ለሚመለከተው አካል እናቀርባለን፡፡ እርፍ! ልማድ ሆኖ እንጂ እጥር ያለች መልስ እያለች ዙሪያ መሄድ ለምን እንዳስፈለጋቸው እንጃ! ደግሞ የማይመለከታቸውን የበጀት እጥርት ብሎ መልስ! ህዝቡ ጥያቄውን ያቀረበው እርሳቸው/እነርሱ ፊት ቢሆንም እርሳቸው/እነርሱ ህዝቡን ሆነው ህዝቡን ወክለው ያስተጋባሉ ወይም  ለማሳመን አቅም ካነሳቸው የህዝቡን ጥያቄ (በሰላማዊ ሰልፍ የተገለፀውን) እንደአቅም እንዲጠቀሙበት ይመስለኛል፡፡

አሁን እንዲያው ከዚህ ሁሉ ሥራ የኛ መንገድ ነው የሃገሪቱን በጀት የሚያናጋው ወይ ደግሞ የማህበረሰብ ጥናት፣ የዲዛይን ሥራ የምናምን እያሉ ተስፋ ባልሰጡን፡፡ ለሚቀጥለውስ ለምን የሚል ከሌለ የበጀት እጥረቱን ማን ይቀርፈዋል ደግሞ ሌላ አንገብጋቢ ሥራና አዲስ ምክንያት ይመጣ ይሆናል፡፡

እንደገና ሌላ አንድ የህዝብ ተወካይ መድረክ ላይ ወጡና በፅሁፍ የተዘጋጀውን የአቋም መግለጫ አነበቡ፡፡ በምክትል አስተዳዳሪው መልስ የደበነውን አንጀታችንን የሚያርሱ የአቋም መግለጫዎች በማያባሩ ጭብጨባዎች ታጅበው ተነበቡ፡፡ እነዚህ ጠንከር ሳይሉ አልቀሩም!!

ህዝቡ በተለይም ከዩኒቨርሲቲ የመጡ ተማሪዎች ጥያቄያችን ብዙ ነው፣ መልሱ ግን አጥጋቢ አይደለም ሲሉ ፕሮግራሙ እዚህ ላይ የተጠናቀቀ ስለሆነ እንዳመጣጣችሁ በሰላም ወደየቤታችሁ ሂዱ የሚል ድምፅ ከወደሞነታርቦው አስተጋባ፡፡

ኢቲቪ በነጋታው ላይ ስመለከተው የሳቸውም የኛም ከጀርባ ቀረፃ የተደረገላቸው የህብረተሰቡ ተወካዮችም ንግግራቸው አልታየም አልተሰማም፡፡ ስገምት/ስጠረጥር የርሳቸው ንግግር ሙሉ ሃሳቡ ወጥ ሆኖ አልተቀረፀም… (ሆሆሆሆ ስለተባለባቸው) የኛም ጩኸት ወይ ፍሬ ከርሲኪ ሆኗል (ከሃሳቡ ሳይሆን ከቀረፃ አንፃር) ወይም ጠንከር ሳይል አልቀረም፡፡

እኛም እያጉረመረምን ተ…ለ…ያ…የ…ን…

የሰልፉን ሙሉ ፎቶዎች ማየት የፈለገ በፌስቡክ አድራሻዬ https://www.facebook.com/addisu.bihonegn/media_set?set=a.539837472748527.1073741829.100001668376462&type=3 ገብቶ Demonstration የሚለውን አልበም መጎብኘት ተፈቅዶለታል፡፡

Published by Addisu Bihonegn

I'm a beekeeping Researcher in Andassa Livestock Research Center, Amhara , Ethiopia. BSc in Animal Sciences at Haramaya University MSc. in Apiculture at Bahirdar University.

3 thoughts on “መንገድ መሪ ህዝብ ስለመንገድ ተነሳ!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: