የጉዞ ማስታወሻ – አስከተማ 6-8/11/2005


የጉዞ ማስታወሻ – አስከተማ 6-8/11/2005
ሦስት ባለሙያዎችና አንድ ገንዘብ ከፋይ ሆነን ከሰቆጣ ወደ አስከተማ ለንብ ሥራ እና ለንብና ሳር ግዥ ሄድን፡፡ 8፡00 ሰዓት እንነሳለን ያልነው ስነውደመደም 10፡00 ሰዓት አልፎ ተነሳን፡፡
የንብ ሥራ ያው እንደጅብ በሌሌት ስለሆነ ከምሽቱ 11፡20 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 5፡00 ሰዓት አልፏል (ያው እኩለ ሌሊት በሉት) ስንሰራ አመሸንና በዚያ ምሽት በየምናድርበት ቤት ውሻ እየጮኸብን ሰዎቹንም ከደራው ህልማቸው ቀስቅሰን ገብተን የሞት ሞታችንን ተዘረርን፡፡ ገጠር ስለሆነ አልጋ የለም/አይያዝም፡፡ ብቻ የምታውቀውን ሰው እየፈለግክ ማስቸገር ነው፡፡
በነጋታው ማለዳ ላይ ዕለቱ ሰንበት ነበርና የቤተክርስቲያን ቅዳሴ ከሞትም ከእንቅልፍም አስነሳን፡፡ ሁላችንም እዚያው ስንሳለም ተያየን፡፡
ቁርስ ከተበላ በኋላ አንዱ ባለሙያ (ዓለሙ) እና ገንዘብ ከፋያችን (አስናቀች) ቀደም ባሉ ቀናት የተገዛ ሰምበሌጥ ሳር ለመረከብና ሂሳብ ለመክፈል ማታ ያመሸንበት ቦታ (ወይላ ተፋሰስ ይባላል) ሄዱ
ሁለታችን (እኔ/አዲሱና መረሳ) የሚገዙ ንቦች ወደሚገኙበት ቦታ (ይሄ ደግሞ ደብረ ወይላ ይባላል) አርሶአደሮች መንገዱን እየመሩን ልንሄድ ተስማማን፡፡ ልብ በሉ የተስማማነው ግን የ45 ደቂቃ መንገድ ነው ስላሉን አይከብደንም ብለን ነው – ለሞራልም ለጤንነትም ብለን፡፡
45 ደቂቃ ሲሉን እውነት መስሎን በበጀግና ዕርምጃ በ30 ደቂቃ ፉት ልንላት አስበን አጀማመራችንን ፈጠን አደረግን፡፡ ከመሪ አርሶ አደሮቻችን ጋር የባጥ የቆጡን እየቀባጠርን ቀጠልን፡፡ኧረ ተውኝ ልክ ቦታው ስንደርስ ብናሰላው 2፡05 ፈጀብን፡፡ ለካ በግንጭላቸው ነበር ያሳዩን… “ይቺን ተራራ አልፈን…” ብለው፡፡ ሰዓቱን የሚነግሩን ግን አፋቸው እንደገባ ወይም በራሳቸው ግምት እንጂ ሰዓት ተይዞለት አይደለም፡፡ ኧረ እንኳን በእጃቸው ወይም በበትራቸው አልጠቆሙን… አንድ ቀን ወይም ሁለት ቀን ሲሆን እንዲያ ያመላክታሉ አሉ – ባገርኛው!
ያንን ወገብ በጣሽ አቀበትና ደፍቶ ጣይ ቁልቁለት ስንለው ስንለው መንገድ የማናውቅ እስኪመስለን ድረስ ስልችት ብለን ላብ በላብ ሆነን ገባን፡፡
መጀመሪያ ለግዥ ወደተስማማንባቸው ንቦች ስንሄድ ከአንዲት ልጅ እግር በቀር ትልቅ ሰው የለም፡፡ ልጅቱ ውሻዋን ይዛልን ወደ ውስጥ ዘለቅን፡፡ ንቦቹም (እንደከተማ ጠጪ-ያላበው ቢራ እንደሚወደው) ያላበው ይወዳሉ ተቀበሉን፡፡ ግራ ቀኝ ሲያጣድፉን የሚነደፍ አካላችንን ሸፋፍነን ሩጫችንን ወደመጣንበት እግሬ አውጪኝ… ነካነው ልበል አስነካነው፡፡
ወደሌላኛው ንብ ወዳለበት ቤት (ደግሞ ሌላ ተራራ… ወደ 20 ደቂቃ ይሆናል) ሄድን፡፡ ኧረ መመለሻንን ያየ? ደርሶ መልስ 4፡50 መሆኑን አስተውላችኋል? ለነገሩ ብታስቡትስ እናንተ አንባቢ እንጂ ተራማጅ አይደላችሁ
ባገሩ ሰው የለም፤ ውሾች መግቢያ አሳጡን ኧረ መውጫም አልሰጡን፡፡ በተለይ አንዱ የቤተመንግስት ወታደር ሆነብን-ግግም! አንዱ አርሶ አደር የሚያውቃቸው ሰዎች ቤት ተጠጋን…ውሾቹ ግን ባሰባቸው፡፡ ያ የቤተመንግስት ታማኝ እልኩ ሲጨምር ጥርሱ ሲያድግ ይታያል፡፡ የቤቱ ባለቤት ውሻ በተቃራኒው እቤቴ የገቡትን አትነኩም በሚል የጨዋ አደግ መልሱን ወደነሱ ያስተጋባል፡፡
እንደምንም ውሾቹን የሰው ያለህ ብለን ንቦቹ ጋ ገባንና የምንፈልጋቸውን ምልክት አድርገን ወጣን፡፡ ደግሞ መውጫ ልመና…አሁንስ ጠንቶባቸዋል!
እኔ ግን ደሜ ፈልቶ ውሻውን በገዛ ሃገሩ ሄጄ አላላውስ ስላለኝ ስንመለስ ድንጋይ ላጎርሰው ሁለቴ ብወረውር ሳትኩት (ያውም በልጅነቴ ስንትና ስንት ግልገልና ዶሮ በቀለጠምኩበት ግራ እጄ)
መንደር ውስጥ ሰው ብናጣም አሉ የተባሉትን የንብ መንጋዎች ካየን በኋላ መሪዎቻችን አርሶአደሮች እዚያው ቀርተው፣ ማታውኑ እንዲያመጡልን ለባለቤቶቹ ነግረው፣ ለወጣቶች (ሥራ አጥ ሞልቷል) አሸክመው እንዲያስመጡ ተማምነን ወደ ቤተክርስቲያን ሄዱ፡፡
ለካ ይሄን ሁሉ መንደር ስንዞር ትልቅ ሰው ያጣነው ወደ ቤተክርስቲያን ሄደው ነው፤ ሰንበቴ ሊጠጡ… ያን የደጋ ኮረፌ እፍፍፍ እያሉ ሊያፍሱት፡፡ መቼም መሪዎቻችን ያን ኮረፌ አይለቁትም! ቶሎ ወደ ከተማ በገባንና እኛም ገዝተን በጠጣን ብለን ፎከርን፡፡
ፊታችንን ወደተነሳንበት አዞርን… መንገዳችንን ጀመርን፡፡ ያሳለፍነውን፣ ያየነውን፣ የታዘብነውን ምኑንም ምኑንም እያወጋን፡፡ መሃል ላይ መንገድ ስተን ኖሮ አንድ ተራራ ከፍ ብለን ቅድም የመጣንባትን መንገድ ቁልቁል አየናት፡፡ ምልክት ያደረግነው ደግሞ አንዱ አርሶ አደር የእናቴ እርሻ… እያለን የነበረውን ነው፡፡ ከተራራው አናት ወደ ‘የእናቱ እርሻ’ እንጨት ሳሩን እየጨመደድን፣ እየቧጠጥንም፣ እየተንፏቀቅንም ቁልቁል ወረድን፡፡
አሁን ከተማው ሩቅ ቢሆንም ይታያል፡፡ በጣም ደክሞናል በጣም፤ ርቦናል፡፡ የርሃብ ማስታገሻ የደደሆ ፍሬ እየሸመጥጠን ጋምነው፡፡ አይ ሲጥም ሲርብ የተገኘ! ትንሽ አለፍ እንዳልን ጓደኛዬ የሆነ ነገር አይቶ በዱላው ነካ ነካ አድረጎ እንዳየው ጋበዘኝ፤ አየሁት- የዝንጆሮ ሰገራ/በጠጥ ነው- ተያይተን ተሳሳቅን፡፡ ይሄ ምን ያስቃል እንዳትሉ፡፡ ዝንጆሮዋ የበላቺው (ከሰገራው እንዳረጋገጥነው) የደደሆ ፍሬ ነበር፡፡ ጥሞን የበላነው ፍሬ ጎመዘዘን፡፡ እንዲያም ሆኖ ሳቃቺን አላባራም፡፡ በሳቃቺን መሃል እንደገና መንገድ ስተን ወንዝ ውስጥ መግባታችንን ስናይ የቀረቺው ጉልበታችን ፈሰሰች፡፡
አሻግረን ከወንዝ ማዶ ያሉ ሁለት ሰዎችን ስንጠይቅ መንገዱ ከተነሳንበት አቅጣጫ ሌላ ነገር ግን የተሻለና ቅርብ እንደሆነ.. እንዲያውም አብረውን እንደሚሄዱ ሲነግሩን እፎይታ ተሰማን፡፡ ቀለለን፡፡
እናላቺሁ ወንዝ ለወንዝ እየሄድን በጉዟችን መሃል አንዱ ሰውዬ (ኋላ ስም ስንለዋወጥ ተስፋዬ ብሎናል) እኛን እንደሚያውቀን ሰቆጣ 14 ዓመት እንደኖረ ሲነግረን ግር አለን፡፡ እኔ ግን ወሬ ለማዋራትም ይበልጥ ለመተዋወቅም ይበጃል ብዬ ‘እኔ ግን የማውቅህ ይመስለኛል፤ አናፂ ነህ?’ አልኩት – በግምት ሳየው አናፂ ስለመሰለኝ:: በለሳኝነት ሞያ እንደኖረ፣ ይባስ ብሎ የኛ መኪና የሶስት ዓመት ልጁን ገጭቶ ገድሎበት ሃገር ጥሎ እንደመጣ፣ ስላሟሟቷ ሲተርክልን ጭራሽ አሳዘነን፡፡ በአንድ በኩል እንኳንም የሾፌሩ ወንድም ወይም ዘመድ አልሆንን፡፡ ማን ያውቃል ደሙ ቢፈላስ! ይህን ወሬ እየኮመኮምን ከንፈራችንን እየመጠጥን የከተማው መግቢያ አቀበት ላይ ስንደርስ ዝናብ ጣለ፡፡ በምን አቅማችን እንሩጥ፤ እንኳን አቀበት በደከመ ጉልበት ልንሮጥ አካሄዱም ጠፋን፡፡ ዝም ብለን እየተደበደብን ልክ ከተማ ስንገባ ዝናቡም አባራ፡፡ ታዲያ ይሄ የትዕዛዝ አይባልም – ለነገሩ ለቀለብላባማ ይበለው፤ ሲያቀብጠን ነው፡፡ 8፡20 ሆኗል፡፡
ልንለያይ ስንል ተስፋዬን ‘በል ድካም የሚያወጣ ቆንጆ ኮረፌ አሳየን’ አልነው፡፡ በሚያውቀው መርቶ ይዞን ሄደ፡፡ ኮማሪዋ ሦስት ብቻ የሚሆን እንደቀራት ስትነግረን ደስ ብሎን ገባን፡፡ ኮረፌው ሲቀዳ አረፋው ቀድሞ ኩባያውን ሞላው፡፡ እፍፍፍ እያልን ለጋነው፡፡ ስላረፍን ይሁን ስለጠጣን አላውቅም ድካማቺን ቀለለን፡፡ ሂሳብ ከፍለን ወጣን፡፡ ተስፋዬ ግን ካልከፈልኩ ብሎ ተገልግሎ ነበር፡፡ ከሱ ጋር የነበረን ቆይታ እስከዚህ ነበርና ተለያየን፡፡
ከመረሳም ጋር 11፡00 ሰዓት ለመገናኘት ተቀጣጥረን ለጊዜው ግን ወገባችንን ለማሳረፍ ወደያረፍንበት ቤት ሄድን፡፡ እቤት የሚበላም የሚጠጣም ሰጡኝ (የተመራቂ ጓደኛዬ የእንኳን ደስ ያለህ ዝግጅት ስለነበር ሞልቷል ተርፏል) ደመ ነፍሴን በላሁ፤ ጠጣሁ፤ ስተኛ ግን እጄን እንኳን መታጠቤን አላስታውሰውም፡፡ አይ የድካም እንቅልፍ መጣፈጡ፣ አየ የሰዓቱ መሮጡ፡፡ ምንጊዜ ሞባይሌ አላርም እንደጮኸች – ባረቀቺብኝ እንጂ – አቋራጭ!
ዛሬም እንደትናንቱ የምሽት ስራችንን ተያያነው፡፡ ዛሬስ ከድካም ጋር ሆኖ ይመስለኛል የምወደው የንብ ማዛወር ሥራ አስጠላኝ:: 4:45 ሥራው ተጠናቀቀ እንደተለመደው ወደየማረፊያችን ተበታተንን፡፡ እኔ ግን ውሻው ድምፁም ስላስጠላኝ ቀድሜ ደውዬ እንዲይዙልኝ አስጠነቀቅኩ፡፡ ተይዞልኝ ገባሁ፡፡ የደስደሱ ገና እየተጨፈረ ነበር፡፡ ምንም ብደክም ለጓደኛዬ ደስታ ስል የመጨፈሪያ አቅም አሰባስቤ ተወዛወዝኩ፡፡ ለእንቅልፍ ጥሩ ሆነልኝ፡፡ በነጋታው ሁለት ሰዓት የነቃሁት በጓደኞቼ የስልክ ጥሪ ነበር፡፡
ቁርሳችንን በላን፣ ቀሪ ሥራዎቻችንን ሰርተን… ጓዛችንን ጠርፈን… ሰምበሌጥ ሳራችንን ጭነን… ያገራችንን ዘፈን እየዘፈንን ወደሰቆጣችን… በመኪናችን!!
ትዝብቴ ይህችን ታክል ነበረች… ደህና ሁኑልኝ! በሌላ ጉዞ እንገናኛለን!

Published by Addisu Bihonegn

I'm a beekeeping Researcher in Andassa Livestock Research Center, Amhara , Ethiopia. BSc in Animal Sciences at Haramaya University MSc. in Apiculture at Bahirdar University.

2 thoughts on “የጉዞ ማስታወሻ – አስከተማ 6-8/11/2005

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: